በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ጥቅምት 07 ቀን 2015 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
በሚኒስትሩ የእቅድ ክትትልና ግምገማ የስራ ሂደት ኃላፊ ተመስገን ተሰማ፤ በዘንድሮው በጀት አመት ከ450 ቢሊዮ ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሀገር ውስጥ ታክስ 266 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፤ ከወጭ ንግድ የጉምሩክ ቀረጥ ደግሞ ከ183 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱንም በዝርዝር አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 93 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ከሀገር ውስጥና ከወጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ የተገኘ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ሚኒስቴሩ በዘረጋቸው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አሰራሮች የንግዱ ማህበረሰብ በቀላሉ ግብሩን ለመክፈል መቻሉ ገቢው እንዲጨምር አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።
በሐሰተኛ ግብይቶች ላይም የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር መጠናከር ለገቢው መጨመር የራሱ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት የሚሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በአጠቃላይ ከ50 ሺህ በላይ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።