የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞችን መቀበል ጀመረ

243

ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛውን ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተፈጥሮ ሳይንስ ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ዛሬ መቀበል መጀመሩን አስታወቀ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተሰጠ ያለው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የመጀሪያውን ዙር ተፈታኞችን በማስተናገድ በስኬት ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና የሚወስዱ 4 ሺህ 505  ተማሪዎችን እየተቀበለ ይገኛል።

ተማሪዎች የተከለከሉ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ይዘው እንዳይገቡ በጸጥታ አካላት የተጠናከረ ፍተሻና ክትትል እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።

ተማሪዎች በሚኖራቸው ቆይታ የሚያስፈልጓቸው የምግብ፣ የመኝታ፣ የመፈተኛ ክፍሎችና ሌሎች መገልገያዎች በበቂ ሁኔታ መመቻቸታቸውን ዶክተር ከተማ  ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር የተገኙትን ተሞክሮዎች በማጠናከር ፈተናውን ስኬታማ በሆነ መልኩ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ሂደት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በራሱ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ  የጋምቤላ ክልል  ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጀት ናቸው።

ቢሮው በክልሉ የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎችን በቂ ግንዛቤ በማስጨበጡ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች በተረጋጋ መንፈስ መፈተናቸውን አስታውሰው፤ የሁለተኛው  ዙር በተመሳሳይ ሁኔታ ፈተናውን መውሰድ እንዲችሉ ስነ ልቦናዊ ዝግጅት እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተፈታኝ ተማሪዎች ሳይረበሹ ፈተናውን በመውሰድ የድካማቸውን ውጤት ለማግኘት መሰናዳታቸውን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም