በከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ሀገር አቀፍ ፕሮግራም ተጀመረ

78

ሀዋሳ ጥቅምት 5/2015 (ኢዜአ) በከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነ የሚያሳድግ "ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም" የተሰኘ ሀገር አቀፍ ፕሮግራም መጀመሩን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በፕሮግራሙ ዙሪያ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሥራ ሀላፊዎችና ተወካዮች ጋር በሃዋሳ ከተማ እየተወያየ ነው።

ፕሮግራሙ በበጀት ዓመቱ በ11 ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን  የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ጊዜ ገልጸዋል።

የወጣቶችን አቅም በተለያዩ ስልጠናዎች በማሳደግ፣ የስራ ባህላቸውን በመገንባት ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት።

በተለይ በከተሞች በተለያየ ምክንያት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያልገቡና ትምህርታቸውን ያቋረጡ ወጣቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ፕሮግራሙ የወጣቶቹን አቅም በስልጠና በማሳደግና በተለይም በግሉ ዘርፍ የስራ ልምምድ አድርገው ወደ ስራ እንዲሰማሩ የሚደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሙከራ ተጀምሮ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ በሀገሪቱ የሚገኙ 70ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በመድረኩ በፕሮግራሙ ከተመረጡ ከተሞች ከአዳማ፣  ከሀዋሳ፣ ከሻሸመኔ፣ ከጅማ፣ ከድሬዳዋና ከወላይታ ሶዶ ከተሞች የሚመለከታቸው አካላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም