ኪዩር ኢትዮጵያ ለ3 ሺህ 200 ህጻናትና ወጣቶች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን ገለጸ

373

ጥቅምት 5 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኪዩር ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የአካል ጉዳትና ህመም ላለባቸው 3 ሺህ 200 ህጻናትና ወጣቶች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱን አስታወቀ።

ኪዩር ኢትዮጵያ በትላንትናው እለት ለ46 አካል ጉዳተኛ ህጻናትና ወጣቶች ዘመናዊ የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አድርጓል።

የኪዩር ኢትዮጵያ የህጻናት ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዐደይ አባተ፤ ሆስፒታሉ ለህጻናትና ወጣቶች የአጥንትና ቆዳ ህክምና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በተለይም የእጅና እግር ጉዳት ላለባቸው ህፃናትና ወጣቶች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ ማገገሚያ ማዕከላትና ሪፈራል ሆስፒታሎች ተጎጂዎች ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ አስታውሰው በትላንትናው ዕለት ለ46 ህጻናትና ወጣቶች ዘመናዊ የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።

ኪዩር ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለ3 ሺህ ህጻናትና ወጣቶች ነፃ ህክምና የሚሰጥ መሆኑን በማስታወስ በ2015 ዓ.ም ለ3 ሺህ 200 ታካሚዎች ነፃ ህክምና ለመስጠት መታቀዱን ጠቅሰዋል ።

በትላንትናው እለት የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ከተደረገላቸው ህፃናት መካከል በአምቦ ከተማ የሚኖረውና  የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው እንዳለ ተፈራ አንዱ ሲሆን በተደረገለት ድጋፍ መደሰቱን ገልጿል።

አካል ጉዳተኝነት ከመማር፣ ከመስራትና ያለምነውን ከማሳካት አይገድበንም ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

ከህጻንነቱ ጀምሮ በእግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት እጆቹን እንደ እግር በመጠቀም መሬት ላይ እየዳሀ እንዳደገ ወላጅ እናቱ ይናገራሉ።

በዚሁ ሁኔታ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው እንዳለ ከክፍሉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማምጣት ለሽልማት ሲጠራ  “ምናለ መራመድ ችሎ ባየሁት” እያሉ ይተክዙ እንደነበር ነው የሚገልጹት።

በኪዩር ኢትዮጵያ የህጻናት ሆስፒታል የተደረገለት ድጋፍ ይህን ህልማቸውን አሳክቶት በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም