በ36 ሆስፒታሎች ዲጂታል የጤና አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

104

ጥቅምት 4/2015(ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር በዘንድሮው በጀት ዓመት በ36 ሆስፒታሎች ዲጂታል የጤና አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ "ዲጂታል ጤና-የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ" በሚል መሪ ሃሳብ ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን "የዲጂታል ጤና" ሳምንት ዛሬ አጠናቋል።

የዲጂታል ጤና ሳምንቱን ማክበር ያስፈለገው ለሕብረተሰቡ የጤና ፍላጎት በተሟላ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ለተግባራዊነቱ በጋራ ለመሥራት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ ማድረግ ከተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የጤና አገልግሎት ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ማዘመን ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም ይህን በማስፋት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 36 ሆስፒታሎችን በዲጂታል ጤና ሥርዓት ለማቀፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዲጂታል የጤና ሥርዓት ታካሚዎች የእጅ ስልካቸውን ተጠቅመው በሚዘጋጀው የጤና መተግበሪያ በመግባት ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቀላሉ መረጃ እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

የህክምና ውጤታቸውን ማሳወቅን ጨምሮ ሌሎች ፈጣን አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ዶክተር አየለ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ህሙማን የሚታከሙበትን የሕክምና ተቋም ለመለየትና የሚያክማቸውን ሐኪም ለማግኘት የሚያጋጥማቸውን እንግልት እንደሚያስቀርም ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል የጤና ሥርዓት የጤና ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛልም ነው ያሉት።

የዲጂታል ጤና ሥርዓት የተጠያቂነት አሰራርን እውን ለማድረግም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸው አገልግሎቱን ለመጀመር አስፈላጊ መሰረተ-ልማቶች በመሟላት ላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም