የውጭ ባንኮች መግባት ...

577

በኢትዮጵያ በ1901 ዓ.ም የባንክ አገልግሎት መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከኢትዮጵያ ባንኮች በተጨማሪ የውጭ ባንኮች እ.አ.አ እስከ 1970ዎቹ ድረስ በአገር ውስጥ ይንቀሳቀሱ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ስር ነቀል ለውጥ ተካሂዶ ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የውጭ አገር ዜጎች ባንኮች ዘግተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። አገሪቷ ከምትከተለው የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የተነሳ የውጭ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል። ይህ ሂደት በኢህአዴግ መንግስትም ቀጥሏል። የኢኮኖሚ ባለሙያና አማካሪ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደሚገልጹት ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ባንክ ለመመስረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሊኖረው እንደሚገባ በህግ ተደነገገ።

ባለሙያው ከኢትዮ-ቢዝነስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ መንግሥት የውጭ አገሮች ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ውስጥ ገብተው መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ተፈቀዷል።  በዚህ ስርዓት “ባንኮች መግባታቸው የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል” ብለዋል። የውጭ አገሮች ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት አገሪቷ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲኖራትና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ለማሳደግ እንደሚያስችላል ተስፋ ያደርጋሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ በአነስተኛ ወለድ ብድር ለማግኘትና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተለምዶ ሲሠራበት የነበረው የባንክና የመድን አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ጭምር ትልቅ ዕገዛ ሊያደርግ ይችላል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከ20 በላይ ባንኮች ይገኛሉ። እነዚህ ባንኮች በቁጥር ደረጃ ከፍተኛ ይሁኑ እንጂ በካፒታል አቅማቸውና በአደረጃጀታቸው በዓለም ዓቀፍ መለኪያ ዝቅተኛ ስለመሆናቸው ነው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ የሚያመለክቱት።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከሰሃራ በታች ከደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ቀጥሎ ሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ የሚባለው የኢትዮጵያ ነው። የኢትዮጵያ ባንኮች ግን በኢኮኖሚው ደረጃ ልክ ያደጉ አይደሉም። ይህም የኢኮኖሚ እድገት ግቡን በእነዚህ የግል ባንኮች ብቻ ማሳካት አይችልም።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጭ በተጨማሪ እነዚህ በአገር ውስጥ የሚገኙ የግል ባንኮች ጠቅላላ ሀብታቸው ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ባለሙያው፤ ኢትዮጵያ እንድታድግ ከተፈለገና የውጭ ቀጥታ  ኢንቨስትመንት ለመሳብ የውጭ ባንኮች መግባት አስፈላጊ ነው። የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ግን ቀድሞ በተሰራ ህግና ስርዓት መበጀት ይኖርበታል። በአፍሪካም እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ያሉ አገሮች የውጭ ባንኮችን ወደ አገራቸው በማስገባት አገራዊ ኢኮኖሚያቸውን ማነቃቃት ችለዋል። “በዘርፉ ከተሰማሩ ባንኮች ውጭ የውጭ ባንኮች ሲገቡ ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና   መንገድ ቢገቡ ተመራጭ ይሆናል” ሲሉም ነው ያስረዱት። በዚህም የገንዘብ አቅም ማሳደግና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ለሚችሉ ባንኮች ቅድሚያ  ቢሰጣቸው ተመራጭ እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ አጽነኦት ሰጥተው እንደገለጹት፤ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ መግባት በፋይናንሱ ዘርፍ የሚታየውን የስራ ባህልና አስተሳሰብ በማምጣት በንግዱ ዓለም ላይ የጎላ ሚና ይኖረዋል። እስካሁን ከአፍሪካ ውጭ ያሉ ባንኮች ምንም ፍላጎት ባያሳዩም እንደ ደቡብ አፍሪካና የናይጄሪያ እና የኬንያ ባንኮች ፍላጎት አሳይተዋል። በዚህም እንደ አገር የሚመጡትን ታሳቢ በማድረግ የመተዳደሪያ ህጎችን አዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባል።

በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ባንኮችን በማጠናከር ጠንካራ ባንክ እንዲሆኑ ለማስቻል በቁጥር ብዙ የሆኑትን ወደ ትንሽ ቁጥር ሰብሰብ ብለው የተሻለ አስተዳደራዊና ካፒታላዊ አቅም መፍጠር ይገባል።

ኢኮኖሚስቱ የአፍሪካ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የባለሙያዎችና ከዘርፉ እንዲሁም ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ግለሰቦች ዘንድ ውይይት መደረግ ይገባዋል።  ውይይቱ እነማን ባንኮች ይመጣሉ? ምን የተሻለ ነገርስ ይዘው ይገኛሉና ምን መደረግ አለበት? የሚለውን መመለስ ይችላል።

“እነዚህ ባንኮች ሲገቡ የውጭ ምንዛሬ ችግርን ከሚቀርፉት በላይ ትልልቅ አገራዊ የልማት ድርጅቶች ብድሮችን በማበደር ሀብት ማሰባሰብና ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የአገር ውስጥ ባንኮችን ያቀጭጫል” ሲሉም ይሞግታሉ።

ለዚህም የውጪ ባንኮች ይግቡ ሲባል ከብሄራዊ ባንክ በተጨማሪ ሌሎች ገለልተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲዎች መቋቋም ግድ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረመድን ናቸው። በዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ደረጃ የሰለጠነ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ ሊያሳድጉ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። “ፋይናንስ ዘርፉን የሚደግፍ  እና በርካታ ማሠልጠኛ ተቋማት  አለመኖራቸው የፈጠረው ክፍተት ቀላል ባለመሆኑ በዚህ ላይ ብዙ መስራት ይጠይቃል” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በቻርተር ባንክ ደረጃ የበቃ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ውስን በመሆኑ ችግር ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ የኢትዮጵያ ባንኮች ከዓለም የግብይት ቋንቋ ሥርዓት ጋር ራሳቸውን፣ ሠራተኞቻቸውን እያበቁ አይደለም። ስለሆነም  “የውጭ ባንኮች ሲገቡ ሊፈተኑበት ይችለሉ” ብለው እንደሚያምኑ ነው አቶ አሰግድ የሚገልጹት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን “የሥራ መሪዎችንም ሊመለከት ይችላል” የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሁን ባለው አቅም በውህደትና በጥምረት የአገሪቷን ባንኮች ብቁ ሊያደርጉ የሚችሉ ዕድሎች ስላሉ በዚህ መጠቀሙ ተመራጭ እንደሚሆን መክረዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚያመለክቱት፤ የአገር ውስጥ ባንኮች በብዛት ያገለግሉ የነበረው ከፍተኛ የንግድ ተቋማትንና ግለሰቦችን ነው። መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት የውጭ ባንክችን የማስገባት ውሳኔ ተጨማሪ ተወዳዳሪ ስለሚሆኑባቸው ይህንን መካከለኛ እና ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያለውን ማህበረሰብ ዋነኛ ደንበኞቻቸው አድርገው ሊመጡ ቢችሉ መልካም ስለመሆኑ ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ “የባንክና ፋይናንስ ተቋማት አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል አዲስ አሰራር መከተል ይገባቸዋል” ያሉት ደግም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ዳኪቶ አለሙ ናቸው።

ዶክተር ዳኪቶ አለሙ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ግሎባላይዜሽን በተስፋፋበት ሁኔታ የፋይናንስ ስርዓቱን በር ዘግቶ በመቀመጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም።  ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግ ማቀዷ ተገቢነት አለው። በአገር ውስጥ ባንኮች ብቻ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት መገንባት እንደማይቻል ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ለውጭ ባንኮች በራቸውን ክፍት ያደረጉ የአፍሪካ አገሮች በኢንቨስትመንት ፍሰትና ሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ ስልመሆናቸውም ያስርዳሉ።

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከካፒታል ገበያ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘቱም በላይ ባንኮች ይዘውት የሚመጡትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የአገር ውስጥ ባንኮችም ማግኘት ከቻሉ ተወዳዳሪ ከመሆን ባለፈ የተሻለ እድገት የማስመዝገብ እድላቸው ሰፊ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምትገነባው ግዙፍ ኢኮኖሚ የባንክ ዘርፉን ማጠናከር ወሳኝ ነው። ይህ ለውጭ አገሮች ክፍት ለማድረግ የተፈቀደው ፖሊሲ በቂ የዝግጅት ጊዜ መስጠት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከር፣ የውጪዎቹ የሚገቡበት መንገድ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተትበት መመሪያ ማውጣት ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም