የኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትን ወደ አዳዲስ የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት ይሰራል

210

ጥቅምት 3 ቀን 2015 (ኢዜአ)የኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትን ለማሳደግ ከዚህ በፊት ቡና አብቃይ ወዳልሆኑ የክልሉ ዞኖች ለማስፋት እንደሚሰራ ገለጸ።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰአዳ አብዱረህማን እንደተናገሩት ቡና የክልሉ የኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ ቡና አብቃይ ያልሆኑ ዞኖች ጭምር ማስፋት ያስፈልጋል።በጅማ ዞን 'የቡና ቀን' ማጠቃለያን ምክንያት በማድረግ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ተካሂዷል።

አፈ ጉባኤዋ በዚሁ ወቅት በተለይም የቡና ምርትን ለማሳደግ ቡና አብቃይ ያልሆኑ አካባቢዎችም ወደ ቡና ልማት መግባት አለባቸው ብለዋል።

በክልሉ የቡና አምራች ከሆኑ ዞኖች መካከል ጅማ ዞን ዋነኛዋ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ የቡና ዘሮችንና ልምድ በመለዋወጥ በሌሎች አካባቢዎችም የቡና ልማትን ማስፋፋት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ሲሆን የቡና ምርት የክልሉን አጠቃላይ ኢኮኖሚ የሚደግፍና ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል።የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከ57 ሺህ ቶን ቡና በላይ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል።

አሁን ለሚሰበሰበው የቡና ምርት የዘርፉ ሙያተኞች፣ ባለሀብቶችና አምራቾች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

በዞኑ 374 የቡና መፈልፈያ ቦታዎች መኖራቸውን ገልጸው በተለይም የቀይ ቡና አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለመቅረፍ የቡና ባለሞያዎችና አርሶ አደሮች ተኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ቡና በዞኑ የሚታወቅ እና የህዝቡ የኢኮኖሚ መሰረት ከመሆኑ አንጻር ከጥራትም ሆነ ምርትን በማሳደግ በርካታ ስራዎች የሚጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከወይይቱ ተሳታፊወች መካከል የጌራ ወረዳ ግንባር ቀደም አርሶ አደር አባተማም አባወሊ፤ ቡናን አምርተው ውጭ አገር በመላክ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራሉ።

ከውይይቱ በኃላ በዞኑ የሚመረቱ በምርምር የተዳቀሉ የቡና ዝርያዎች እንዲሁም ነባሩ የተፈጥሮ ቡና ዘሮች ተጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም