በጉጂ ዞን በሁለት ወረዳዎች 25 ሺህ ለሚጠጉ ህጻናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ተሰጠ

81

ነገሌ ጥቅምት 2/1015 ዓ.ም /ኢዜአ /በጉጂ ዞን በሁለት ወረዳዎች 25 ሺህ ለሚጠጉ ህጻናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ክትባቱ የተሰጠው በዞኑ የጸጥታ ችግር በነበረባቸው ሁለት ወረዳዎች መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። 

በሁለቱ ወረዳዎች ከ24 ሺህ 900 የሚበልጡ ህጻናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውም ተመልክቷል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የህብረተሰብ ጤና ስጋት መከላከል ባለሙያ አቶ ገላና ጥላዬ እንደገለጹት ክትባቱ የተሰጠው በዞኑ ሊበንና ጉሚ ኤልደሎ ወረዳዎች ነው፡፡

በተደረገው የቤት ለቤት የክትባት መርሀ ግብር ክትባቱን ለ22 ሺህ ህጽናት ለመስጠት ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡  

በተካሄደው የክትባት መርሀ ግብር ዘመቻ ከአምስት አመት እድሜ በታች የሆኑ 24 ሺህ 994 ህጻናት ክትባቱን ወስደዋል ብለዋል፡፡

የአካባቢው ሕዝብ በጤና ዙሪያ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ በመምጣቱ ከእቅድ በላይ 2 ሺህ 294 ህጻናት መከተባቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉጂ ዞን የጸጥታ ስጋት በሌለባቸው 16 ወረዳዎች 383 ሺህ 683 ህጻናት በመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም