በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል - ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ

543

ጥቅምት 1/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለተነሳው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በታሰበው ሕዝበ ውሳኔ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በዚህ ውይይት ላይ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ሕዝበ ውሳኔውን  ማስፈጸም የሚችልበትን እቅድ ይፋ አድርጓል።

በቦርዱ እቅድ መሰረት በደቡብ ክልል ሥር ባሉት ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ የሕዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ  ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ የይሁንታ ውሳኔ ማሳለፉም ተመላክቷል።

የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ እንዲሁም የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች ሕዝበ ውሳኔው ተፈጻሚ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል የሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕግና አሰራርን ተከትሎ እንዲከናወን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ሕዝበ ውሳኔውም በሕግ አግባብ ደረጃውን በጠበቀና እውነተኛነቱን ባረጋገጠ መልኩ የሕዝብን ሃሳብ በመለካት ለማሳወቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የቦርዱ የኦፕሬሽን አማካሪ ብሩክ ወንድወሰን፤ የህዝበ ውሳኔ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት ለህዝበ ውሳኔው 18 ሺህ 885 ሰዎች በአስፈፃሚነት እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ የህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ማዕከል የምትሆን ሲሆን የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በቦርዱ ጊዜያዊ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ ቀንን አስመልክቶ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮችን፣ የአደረጃጀት ሂደትን፣ የድምጸ ውሳኔ፣ ምርጫ አሰጣጥና አፈፃጸምን በሚመለከት ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም