በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

126

መስከረም 30/2015 (ኢዜአ) በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በሎስ አንጀለስና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሃብቶች ጋር ውይይት አደረጉ።

ትናንት በተደረገው ውይይት በኢትዮጵያ ስላሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የኢኮኖሚና ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች መንግስት ቀድሞ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት የኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መወሰዱን ገልጸዋል።

በመንግስት ስር የነበሩ ኩባንያዎችን ወደ ግል ዘርፍ ማሸጋገር፣ እንደ ፋይናስ፣ ቴሌኮም፣ ኢነርጂ እና መሰል ዘርፎችን የውጭ ባለሀበቶች ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድን ለአብነት አንስተዋል።

ከውጭ የሚገባውን የምግብ ነክ አቅርቦት በአገር ውስጥ አቅም ለመተካት ብሎም ወደወጭ ገቢያ ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ስለሺ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተቀናጀ የስንዴ ምርት ውጤቶች የተያዘው እቅድ እንደሚሳካ አመላካች መሆኑን ተቅሰዋል።

በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሰፊ የሰው ኃይል፣ አመቺ የአየር ሁኔታ፣ ለገበያ አማካይ የጅኦግራፊ አቀማመጥ፣ ሰፊ የመሬት አቅርቦት፣ የታዳሽ ኃይል መሰረተ ልማቶች ለባለሃብቶቹ ስራ ስኬት ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።

"በተለይ በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራዎች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ከኢንቨስትመንት ተሳትፎ ባለፈ አገር ይህን ፈታኝ ወቅት በምታልፈበት ወቅት አለኝታነትን ማረጋገጥ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ባለሃብቶቹ ከመነሻው ጀምሮ ወደ ስራ እስኪገቡ ድረስ ኤምባሲው ከአገር ቤት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ በግብርና ልማት፣ በውሃና ኢነርጂ፣ በቴሌኮም፣ በጤና፣ በቡና ልማት፣ በሎጂስቲክስ፣ ፋይናንስ፣ በምርምር እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም