የታክሲ አሽከርካሪዎችና ተራ አስከባሪዎች የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን ያድሳሉ

78
አዲስ አበባ  መስከረም 12/2011 የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች እና ተራ አስከባሪዎች ማህበር አስር የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን ለማደስ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ። የማህበሩ አባላት የበጎ ፍቃድ ቤት እድሳቱን የሚያከናውኑት በመጪዎቹ ወራት ውስጥ መሆኑን የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገልጿል። ባለፈው ክረምት በአዲስ አበባ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተያዘው ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል። የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ባለፉት የክረምት ወራት በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ ተግባራት በከፋ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 246 ቤቶችን በማደስ ለነዋሪዎቹ ማስረከብ ተችሏል። የታደሱት ቤቶች ድህነት የተጫናቸውና እርዳታ የሚሹ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚኖሩባቸው በርካታ የመዲናዋ ገፅታዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በበጎ ፈቃደኝነት የተጀመረውን ይህንን አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ሥራ ማስቀጠል እንዲቻል የከተማው ታክሲ አሽከርካሪዎች እና ተራ አስከባሪዎች  የድርሻቸውን ለመወጣት የላቀ ፍላጎት እንዳላቸው ለከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታውቀዋል። የቢሮው የወጣቶች ንቅናቄ ተሳተፎ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ትዕዛዙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማህበሩ አባላት በየክፍለ ከተማው አንድ ቤት በጥቅሉ 10 ቤቶችን በጥሩ ሁኔታ አድሶ ለማስረከብ ከቢሮው ጋር ተስምተዋል። ማህበሩ እያሳየ ያለው ይህ የበጎ ፈቃድ ተግባር ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም በአቅማቸው የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን በመግለፅ ለማህበሩ አባላት ምስጋና አቅርበዋል። የአቅመ ደካሞችን መርዳትን ጨምሮ ለአገርና ዜጎች ህይወት መሻሻል የሚፈይዱ የበጎ ተግባር ሥራዎችን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አቶ አክሊሉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ የተፈጠረው መነቃቃት በአገሪቱ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ባህል የሚሆንበትን መሰረት እየጣለ እንደሆነ ይነገራል። በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ስርዓትና ተቋማዊ መልክ ተበጅቶለት በዘላቂነት የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዲመቻች ብዙዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም