በውሀ እጥረት ተቸግረናል--- የአሶሳ፣የአርባምንጭና የጭሮ ከተሞች ነዋሪዎች

120
አሶሳ/አርባ ምንጭ/ጭሮ ግንቦት 11/2010 በአካባቢያቸው ባጋጠማቸው የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረት መቸገራቸውን የአሶሳ፣ የአርባ ምንጭና በጭሮ ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። በአሶሳ ከተማ  በተለምዶ ገብርኤል በሚባለው  አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ደስታ ጃራ እንዳሉት የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ከተቋረጠ ሁለት ወራት ሆኖታል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በቦቴ እያከፋፈለ ያለው ውሀ ስለማይዳረስ ከሌላ አካባቢ ለሚቀዱት አንድ የባለ 25 ሊትር ጀሪካን ውሀ አምስት ብር እየከፈሉ ለመጠቀም መገደዳቸውንና  እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል ። በከተማው የመናኸሪያ አካባቢ ነዋሪ አቶ ትዕዛዙ ደንድር በበኩላቸው የውሃ እጥረቱ የተከሰተው ከጥር ወር ጀምሮ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ " የቧንቧ ውሃ በሳምንት አንዴ ቢመጣም በበቂ ሁኔታ ሳንቀዳ ተመልሶ ስለሚጠፋ ተቸግረናል"ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃሩን መንሱር ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  በከተማው የውሃ አቅርቦት በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። " ከአምስት ዓመታት በፊት የከተማውን 20 ሺህ ነዋሪ ታሳቢ በማድረግ የተሰራው የውሀ ማስፋፋፊ ፕሮጀክት አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የነዋሪው ቁጥር በእጥፍ በማደጉ እጥረቱ ተፈጥሯል " ብለዋል ። በተያዘው ዓመት አጋማሽ ላይ ሁለት የውሃ ጉርጓዶች መድረቃቸውና ሌሎች ጉርጓዶች የሚያመርቱት ውሃ መቀነሱ ደግሞ እጥረቱን እንዳባባሰው አመልክተዋል፡፡ "ጽህፈት ቤቱ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት የውሃ ስርጭቱን በፈረቃ በማከፋፈል ላይ ነው "ያሉት ስራ አስኪያጁ ስርጭቱ በማይዳረስባቸው አካባቢዎች በቦቴ ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩ የሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ ስራ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የስድስት ጥልቅ የውሃ ጉርጓዶች ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝና በቀጣይ ዓመት እስከ ህዳር ወር ድረስ ግንባታውን ለመጀመር እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ የውሃ እጥረት ከተከሰተ ከሁለት ወር በላይ በመሆኑ መቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ  ሼቻ ክፍለ ከተማ ቤሬ ቀበሌ ነዋሪ  አቶ ደርብ ገሠሠ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳመለከቱት  ከዚህ ቀደም  በሣምንት ሶስት  ጊዜ ይመጣ የነበረው የቧንቧ ውሀ አሁን ላይ በ15 ቀን አንድ ጊዜ ብቻ መምጣት ጀምሯል ። ውሀ ከሌላ አካባቢ ለማምጣት ለትራንስፖርት ጨምሮ ከፍተኛ ወጭ እያወጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ። በክፍለ ከተማው የጫሞ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ ዓባይ በበኩላቸው  ውሃ ፍለጋ ሰፊ ጊዜ እያባከኑ  የዕለት ተዕለት  ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ አለመሆናቸውን ተናግረዋል ። በአካባቢየቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ ይመጣ የነበረው የቧንቧ ውሀ ለሁለት ወር ያክል በመቋረጡ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ከሌላ አካባቢ ለመቅዳት መገደዳቸውን የተናገሩት ደግሞ በነጭ ሣር ክፍለ ከተማ የዕድገት በር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቤቲ ታምሩ ናቸው፡፡ የአርባ ምንጭ ከተማ ውሃና ፊሳሽ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ አብርሃም   ላለፉት ሁለት ወራት ያጋጠመው የውሃ እጥረት ከኃይል አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገልግሎት የሚሰጡ ሶሰት የውሃ ፓምፖች ቢኖሩም ባጋጠመ የኤሌክትሪክ ኃይል መቀነስ እየሰራ ያለው አንዱ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል ። " ችግሩን  ለመፍታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አርባ ምንጭ ዲስትሪክት ጋር እየተነጋገርን ነው" ብለዋል ፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአርባምንጭ ዲስትሪክት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ኃላፊ አቶ ገረመው ወንድምሁነኝ በበኩላቸው በዚህ ሳምንት የመስመር ለውጥ የሚደረግ በመሆኑ ችግሩ እንደሚፈታ አስታውቀዋል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በጭሮ ከተማ የኮንዶሚኒየም ሰፈር  ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ  ኤልሳቤጥ ለገሰ የውሃ አቅርቦት እንደተቋረጠባቸውና ለችግር መዳረጋቸውንም ነው የተናገሩት። በአካባቢያቸው  የውሀ ስርጭት ከተቋረጠ 11 ቀናት እንደሆነም ጠቁመዋል። ወይዘሮ አይናለም አበራ በበኩላቸው ንጹህ የመጠጥ ውሃ በመጥፋቱ ምግብ ለማብሰልም ሆነ የልጆቻቸውን ንፅህና ጠብቀው ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን ገልጸዋል። ለመጠጥ የሚሆን የታሸገ ውሀ  ለመግዛት በመገደዳቸው በገቢያቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸውም ጠቅሰዋል ። " ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ የሚመለከተውን አካል ብናሳውቅም ያገኘነው መፍትሔ የለም"ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አበራሽ ዘመድኩን ናቸው፡፡ የጭሮ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ተወካይ አቶ ጉልላት አማረ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ለከተማውና አካባቢው አገልግሎት ከሚሰጡ ሁለት የጥልቅ ውሀ ጉድግዶች የአንዱ  የውሀ መሳቢያ ፓምፕ በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት በመቃጠሉ ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል ። " እጥረቱን በጊዜያዊነት ለመፍታት ውሀ በፈረቃ እያሰራጨን ነው" ያሉት  አቶ ጉልላት  የተቃጠለውን ፓምፕ የሚተካ ማሽን ከክልል እያስመጡ መሆኑንና ችግሩም  አምስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይፈታል ብለዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም