የኢትዮጵያ መድህንና ደህንነት ያለው በልጆቿ እጅ ላይ ነው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

193

መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) “የኢትዮጵያ መድህንና ደህንነት ያለው በልጆቿ እጅ ላይ ነው” ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

የኢትዮ-ካናዳውያን ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ)፣ ‘ፒፕል ቱ ፒፕል’ እና ‘ሄልዝ ኬር አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያ’ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሕክምና ያዘጋጁት የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል።

በመርሐግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ ተቋማትና ጥምረት ኃላፊዎች እንዲሁም የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍና ትብብር ትልቅ ትርጉም እንዳለው አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ለወገኖቹ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አምባሳደር ታዬ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

“የኢትዮጵያ መድህንና ደህንነት ያለው በልጆቿ እጅ ላይ ነው” ብለዋል።

በመርሐግብሩ በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሕክምና የሚውል ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም