ኮሚሽኑ በወላይታ ዞን በጎርፍ አደጋ ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ ወገኖች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

139

ሶዶ፤ መስከረም 28/2015 (ኢዜአ)፡- የጉምሩክ ኮሚሽን በወላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ የአባያ ሀይቅ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ ወገኖች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በወላይታ ሶዶ ከተማ በመገኘት ድጋፉን ለወላይታ ዞን አስተዳደር አስረክበዋል።

ኮሚሽነሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያውያን ባህል በሆነው መረዳዳትና መደጋገፍ አብረን በመቆም ለጋራ ብልፅግና ልንተጋ ይገባል ብለዋል።

ከተረዳዳን ችግሮችን ልናሸንፍ እንችላለን ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በአበላ አባያ ወረዳ የተከሰተውን ችግር ለመጋራት መስሪያ ቤታቸው ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰብአዊ ድጋፍ ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

'የህብረተሰቡን ሀብት ለህብረተሰቡ' በሚል መርህ በችግር ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ የአሁኑ ድጋፍም ጤፍ፣ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ወተትና የተለያዩ አልባሳትን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ላደረገው ትብብርና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ የተደረገው በክረምቱ ወቅት የአባያ ሀይቅ ከመጠን በላይ ሞልቶ ባስከተለው ችግር ምክንያት ለጉዳት ለተዳረጉ 1 ሺህ 112 አባወራዎች የሚውል መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም