ዩኒቨርሲቲዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በተሻለ ዝግጅት ተቀብለው እያስተናገዱ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

126

መስከረም 28/2015/ኢዜአ/ ዩኒቨርሲቲዎች የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በተሻለ ዝግጅት ተቀብለው እያስተናገዱ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች በበኩላቸው መልካም አቀባበልና መስተንግዶ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን በመቀበል ላይ ይገኛል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የተፈታኞችን የቅበላ ሂደት በዋናው ግቢ ተገኝተው  ጎብኝተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት፤ ዩኒቨርሲቲዎች የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተናገዱ ነው ብለዋል።

ተማሪዎቹን የመቀበል ሂደቱም የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ዕቅድ መሰረት እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችም የተሻለ አቅም እንዳላቸው ያሳዩበት ቅበላ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ተማሪዎችን በየብስና አየር ትራንስፖርት በማጓጓዝ ፈተና ወደየሚወስዱበት ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የተፈታኝ ተማሪዎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅም ከፌደራል ፖሊስና ሌሎች ተጨማሪ የክልል የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተማሪ ወላጆችም ልጆቻቸው ፈተናቸውን በተረጋጋና በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈተኑ አስፈላጊው ሁሉ እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና፤ ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር የሚሰጡ የማህበራዊና ተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ፈተና የሚወስዱ ከ39 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስተናግዳል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ካምፓሶቹ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች የመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ እንዳለም ጠቁመዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎች መልካም አቀባበል ተደርጎላቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲውም ለተማሪዎች ማረፊያ የሚሆን የመኝታ ከፍሎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ አዳራሾችና ምቹ የፈተና ቦታዎችን ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው፤ እየተደረገላቸው ያለው አቀባበል መልካም መሆኑን ገልጸውዋል።

ፈተናቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለመውሰድና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት ማድረጋቸውንም እንዲሁ።

የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የፊታችን መስከረም 30/2015 ዓ.ም በይፋ የሚጀምር ሲሆን በአጠቃላይ 976 ሺህ 18 ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናውን እንደሚወስዱ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም