በመዲናዋ ከ18 ሺህ በሚበልጡ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል-የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ

109

መስከረም 28/2015(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ባለፉት ሶስት ወራት የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ ባደረጉና ሌሎች የንግድ ሕጎችን በጣሱ ከ18 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታወቀ።

የንግድ ቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ስጦታው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴውን ጤናማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ባለፉት ሶስት ወራት ከ95 ሺህ በላይ በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር፤18 ሺህ 818 የሚሆኑት የንግድ ህጉን ተላልፈው ሲሰሩ ተደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡

ቢሮው በእነዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰዱን ነው የተናገሩት፡፡

እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ 5 ሺህ 54  ተቋማት የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው 4 ሺህ 82  ተቋማት ደግሞ መታሸጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ 422  የንግድ ተቋማት  ፈቃዳቸው ሲሰረዝ፣ ሦስት  ድርጅቶች ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸው  መታገዱን  ገልጸው፤፣ 21 ተቋማት  ከንግድ ትስስር እንዲወጡ ተደርገዋል ብለዋል።

ከአስተዳደራዊ ርምጃ ባሻገር በ182  ተቋማት  ላይ ሕጋዊ  ርምጃ  ለመውሰድ ክስ መመስረቱን  ነው የገለጹት።

ሌሎች ቀላል ጥፋት በፈጸሙ የንግድ  ተቋማት ላይ ቀላል ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት  ወደ ህጋዊ የንግድ መስመሩ እንዲገቡ  መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከተላለፏቸው ህጎች መካከል ምርትን በማከማቸት የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ ማድረግ፣ ሸቀጦችን ከተተመነላቸው ዋጋ በላይ መሸጥ፣ ከተመዘገበበት አድራሻ ውጭ መነገድ፣ ካስመዘገቡት የንግድ ዘርፍ ውጭ መስራት እና የምርት ጥራት ማጓደል በዋናነት ይገኙበታል ብለዋል።

የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋትም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ለህብረት ስራ ማህበራት የስራ እንቅስቃሴ መመደቡን ጠቅሰው፤ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትን ቀጥታ ከአርሶ አደሮች ጋር በማገናኘት ምርት በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች  97 የእሁድ ገበያን በማቋቋም  ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም