በምክር ቤቱ የስራ ዘመን የሰላም፣ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

179

መስከረም 27/2015/ኢዜአ/ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመኑ የአገር ሰላም፣ ጸጥታና የደህንነት ጉዳዮች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን በልዩ ትኩረት የሚያከናውን መሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በአዲሱ ዓመት በሚጀመረው 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን ምክር ቤቱ በዋነኝነት ሊያከናውናቸው ያቀደውን ተግባራት በማስመልከት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመኑ የአገር ሰላም፣ የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን በልዩ ትኩረት የሚያከናውን መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ እድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን የማቃለል፣ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠርና ሌሎችም ጉዳዮች በምክር ቤቱ የስራ ዘመን ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል።

በመልካም አስተዳደር ዙሪያም ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አፈ ጉባኤው አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ፣ የታሪክና ሌሎች ልዩነቶች ላይ በዝርዝር በመምከር የጋራ መግባባት ለመፍጠር ለሚከናወነው አገራዊ ምክክር ስኬት ምክር ቤቱ የላቀ ድጋፍና እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያውያን በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ ዓመት የፍትህ አካላት ሪፎርም ተግባራዊ እንዲደረግና የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

ለልማት ጥያቄዎች እቅዶች ማሳካት፣ የፕሮጀክት አፈጻጸምን መከታተልና መደገፍም የምክር ቤቱ ትኩረት ይሆናል ነው ያሉት።

"የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀን" እንዲኖር የማድረግ እቅድ እንዲሁም የአስፈፃሚ አካላትን የመከታተልና የመቆጣጠር እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ስራም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ ህገ- መንግስት አንቀጽ 58 ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት ሁለቱ ምክር ቤቶች ስራ የሚጀምሩት በመስከረም ወር መጨረሻ ባለው ሰኞ እንዲሆን ይደነግጋል።

በዚህም መሰረት የፊታችን ሰኞ መስከረም 30 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት የጋራ መክፈቻ ስነ-ሰርአት የሚካሄድ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አጠቃላይ የ2015 በጀት አመት የትኩረት አቅጣጫዎች በዝርዝር የሚያቀርቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም