የወደሙ 16 ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

232

መስከረም 27/2015(ኢዜአ) የትምህርት ሚኒስቴርና የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ 16 ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ መልኩ ዳግም ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

የዳግም ግንባታ ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና እና በሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጀርመን የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ሰባስቲያን ብራንዲስ ፈርመውታል።

በስምምነቱ መሰረትም በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ 16 ትምህርት ቤቶች በ300 ሚሊየን ብር ወጪ በሰዎች ለሰዎች ድርጅት በዘመናዊ መልኩ ዳግም የሚገነቡ ይሆናል።

አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸው የመልሶ ግንባታ ስራዎች በመንግስት ብቻ መከናወን ስለማይችሉ የሌሎች ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የሰዎች ለሰዎችን ተግባር ፕሮፌሰር ብርሃኑ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር የቀረበለትን ጥሪ በአዎንደታ በመቀበል ለመልሶ ግንባታ አዳዲስ ዲዛይኖችን ሰርቶ በማጠናቀቅ ማስረከቡንም ገለጸዋል።

ለመልሶ ግንባታ ስራው የተለያዩ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦችና ሌሎችም በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር 16 ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የተዘጋጀውን የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ሚኒስትሩ አመስግነዋል።

በጀርመን የድርጅቱ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ሰባስቲያን ብራንዲስ፤ ድርጅቱ ባለፉት 40 ዓመታት የትምህርት ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ከወደሙ ትምህርት ቤቶች መካከል 16ቱን ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው ዲዛይን መሰረት በ300 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም