ለኢሬቻ በዓል ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኬኒያ ልኡክ ባሌ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችንና የስንዴ ልማትን ጎብኝቷል

118

ጎባ መስከረም 27/2015(ኢዜአ)--ለኢሬቻ በዓል ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኬኒያ ልኡክ ባሌ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መሰህብ ስፍራዎችንና የስንዴ ልማትን ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ዞኑ ያለውን እምቅ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የመስህብ ስፍራዎችን ከማስተዋወቅ በተጓዳኝ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የዞኑ አስተዳደር ገልጿል።

ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል አቶ ቦሩ ጉዮ በሰጡት አስተያየት ዓመታዊ የኢሬቻ በዓል ላይ ታድመው ጥሩ ቆይታ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

አጋጣሚውን በመጠቀም በአገሪቱ በተለይ በባሌ ዞን የሚገኙ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የሳነቴ አምባ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጎብኛታቸው መደሰታቸውንም አንስተዋል።

በጉብኝቱ ኢትዮጵያ ከሚነገረው በላይ እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎች እንዳሏት ማየታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የቡድኑ አባል ሙሳ አህመዶ ናቸው።

በተለይ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተፈጥሮ ከታደለ ልዩ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ባሻገር በውስጡ የያዛቸው ብርቅዬ የዱር አራዊቶች ቀልብን የሚገዙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

አቶ ጉዮ አዱላ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ ታሪካዊና የተፈጥሮ መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ መስራት እንደሚጠብቅ አነስተዋል።

መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር በመቅረፍ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የማህበረሰብ አባላቱ በኢሬቻ በዓል ወቅትም ሆነ በባሌ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ባደረጉት ጉብኝት ህዝቡ እንግዳ ተቀባይ መሆኑን መታዘባቸውን ነው የገለጹት።

በተመሳሳይ የልኡካን ቡድኑ አባላት በዞኑ በክላስተር የለማ ስንዴ የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ተስፋ የሚጣልባት አገር መሆኗንም ተናግረዋል።

በዞኑ እየለማ ያለው ስንዴ ኢትዮጵያ ለግብርና ልማት የሰጠችው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን የሚያመላክት ነውም ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው የሉዑካን ቡድኑ ጉብኝት ዞኑ ያለውን እምቅ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ የመስህብ ስፍራዎችን ከማስተዋወቅ በተጓዳኝ የሁለቱን አገራት ወንድማዊ ትስስርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ አመስግነዋል።

በአካባቢው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ሶፍ ኡመር የተፈጥሮ ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴንና የሀርና የተፈጥሮ ደን መገኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አስተዳዳሪው የሉኡካን ቡድኑ አባላት ባዩት የስንዴ ልማትም መደነቃቸውንና ኢትዮጵያ ትልቅ የግብርና ልማት አቅም ያላት አገር መሆኗን መረዳታቸውንም ተናግረዋል።

አዲሱ የኬንያ መንግስት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ለአንድ ቀን ይፋዊ ያስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መመክራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም