ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሰጠቱ በድካማችን ልክ ውጤት ለማግኘት ያግዘናል- ተፈታኝ ተማሪዎች

188

ሆሳዕና፣ አምቦ፣ ሰመራ እና ጋምቤላ (ኢዜአ) መስከረም 27/2015– ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲሰጥ መደረጉ በድካማችን ልክ ውጤት ለማግኘት ያግዘናል ሲሉ በዩኒቨርሲቲዎች ለፈተና የተመደቡ የ12ኛ ክፈል ተማሪዎች ገለፁ።

የዋቸሞ፣ አምቦ ፣ ሰመራ እና ጋምቤላ  ዩኒቨርሲቲዎች   የተመደቡላቸውን  የ12ኛ ክፍል  መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች  እየተቀበሉ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል በሆሳዕና ከተማ የካቲት 25/67 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሙላቱ ሎንሰቆ እንዳለው፣ ፈተናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መሰጠቱ ከፈተና ስርቆት ጋር ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ያስቀራል።   

መንግስት ይህን ለማስቀረት ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ ፈተናው እንዲሰጥ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የገለጸው ተማሪው፣ “ተማሪዎች በድካማቸው ልክ ውጤት እንዲያመጡ ያግዛል” ብሏል።

በራሱ የሚተማመን ተማሪ ለማፍራትና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ መንግስት በትምህርት ላይ የጀመረውን ለውጥ እንዲያጠናክርም ጠይቋል።  

ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈተናውን እንድንወስድ መደረጉ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚናፈስ ወሬ ይታደገናል ሲልም ተናግሯል።

“በተለይ ለፈተና በአግባቡ ሲዘጋጅ ለቆየ ተማሪም የልፋቱን እንዲያገኝ ያደርጋል” ብሏል

ከሆሳዕና ከተማ ዋቸሞ መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ማህሌት ተመስገን በበኩሏ፣ ዘንድሮ ፈተናው በልዩ ሁኔታ መሰጠቱ በፈተናው ላይ ያላት እምነት ከወዲሁ እንዲጎለብት ማድረጉን ገልጻለች።

“ተፈታኞች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው መፈተናቸው ከዚህ ቀደም ከኩረጃና ከፈተና ስርቆት ጋር በተያያዘ ሲነሳ የነበረን ቅሬታ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ” ብላለች።

ተማሪዋ እንዳለችው፣ ከሌላ ሳይጠብቅ በራሱ ሰርቶ ውጤት የሚያመጣና የሚተማመን ዜጋ በብዛት እየፈራ በመጣ ቁጥር በሀገሪቱ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል።

መንግስት የወሰደውን እርምጃ እንደምትደግፈው የገለጸችው ተማሪዋ፣ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የተቀመጠውን መመሪያ አክብራ ለመፈተን መዘጋጀቷን ገልጻለች።

የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሰረቱ በትምህርትና በስነ ምግባር የታነፀ ምክንያታዊ ዜጋን ማፍራት መሆኑን የተናገረው ደግሞ በሀድያ ዞን ጊምቢቹ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ውድነህ ደጀኔ ነው።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መፈተናቸው በራሱ ለሚጥር ተማሪ ፈተናውን በብቃት እንዲያልፍ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጾ፣ “የተማሪን ስነልቦና የሚጎዱ አሉባልታዎችንም ያስቀራል” ብሏል።

ወደፊት ከጠባቂነት ወጥቶ ራሱን የሚችል ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት የሚኖረው ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዳው።

ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በዋቸሞ ዩኒቨርሰቲ የተመደቡ ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲው እየገቡ ነው።

በተመሳሳይ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተማሪዎችም ከትናንት ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲው እየገቡ ነው።

ለተማሪዎቹ በተዘጋጀ ደማቅ የአቀባብል ሥነስርአት ላይ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ባይሳ ለታ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡለትን ተፈታኞች ዋናውን ጊቢን ጨምሮ በሃጫሉ ሁንዴሳ ፣ ጉደር ማሞ መዘምር እና በወሊሶ ካምፓሶች እየተቀበለ ነው።

ለተማሪዎቹ ከተደረገው መስተንግዶ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲውን የማላመድና የስነ-ልቦና ዝግጁነት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረጉላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ነው የገለጹት።

አምቦ ዩኒቨርሲቲው ከ34ሺህ 516 ተፈታኞችን ለማስፈተን የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁ ቀደም ሲል መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የስነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የዩኒቨርሲቲው የስነልቦና መምህራን ገለጹ።

የዮንቨርሲቲው የስነልቦና ትምህርት ክፍል መምህር ወይዘሮ ጸሐይ መኮንን እንዳሉት እንደሀገር ለሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ በቂ የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።

የዘንድሮ ተፈታኞች ከአካባቢያቸውና ቤተሰባቸው ርቀው በዩኒቨርሲቲ የሚፈተኑበት ሁኔታ አዲስና ያልተለመደ በመሆኑ የራሱ ጠቀሜታ ቢኖረውም በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የፍርሀት ስሜት ሊያሳድር ይችላል።  

ይህን ያልተገባ ፍርሃትና ጭንቀት በማስወገድ ለፈተናው ባደረጉት ቅድመ ዝግጅት ፈተናውን በራስ-መተማመን እንዲፈተኑ ስነልቦናቸውን ለመገንባት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

“በእዚህም ከሌሎች የስነ ልቦና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ስለውጤታማ የፈተና አወሳሰድ ዘዴና ማድረግ ስለሚገባቸው ቅድመ ዝግጅት በተመለከ የገጽ ለገጽ ገለጻ ከማድረግ ጀምሮ በራሪ ጽሁፎች ለተማሪዎች አንዲሰራጩ ይደረጋል” ብለዋል።

ፈተና በባህሪው የስነልቦና ጫና ውስጥ እንደሚያስገባ የገለጹት ሌላው የሰመራ ዮኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና መምህር አቶ አብዱ አሊ ናቸው።

“ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ እንዲፈተኑ መደረጉ የፈተና ስርቆትን ከማስቀረት ባለፈ፣ እንደአፋር የጸጥታ ችግር ላለባቸው አካባቢዎች ፈተናን በተረጋጋ መንፈስ እንዲፈተኑ ያደርጋል” ብለዋል

መምህሩ እንዳሉት ተፈታኞች የስነልቦና መረበሽ ሳይገጥማቸው ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በፍጥነት በመላመድ በፈተናው ውጤታማ ለመሆን ራሳቸውን ማዘጋጀት ይገባቸዋል።

ለእዚህም ለተማሪዎቹ የስነ-ልቦናና ተያያዥ ሙያዊ እገዛዎችን በመሰጠት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የሠመራ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሀመድ ኡስማን በበኩላቸው፣ ለፈተናው ስኬታማነት የተቋሙ ሁሉም ባለሙያዎች ያልተገደበ ሁለንተናዊ እገዛ እንዲያደርጉ ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።


የዩኒቨርስቲው የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ከፈተናው በፊት ከተማሪዎች ጋር የገጽ-ለገጽ ውይይት በማድረግ የስነልቦና ዝግጅታቸውን ከፍ የሚያደርጉ ጠቃሚ ምክረ-ሀሳቦችን የሚያስተላልፉበት መድረክ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከ10ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን ዝግጅቱን አጠናቆ ዛሬ ተማሪዎችን በመቀበል ላይ ነው።

የዩኒቨርሲው የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን የተማሪዎችን ቁጥር ታሳቢ ባደረገ መልኩ የምግብ አቅርቦት፣ የመኝታና የመፈተኛ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

ሕፃን ልጅ ለያዙ ሴት ተፈታኝ ተማሪዎችም የህፃናትና የሞግዚት ማቆያ ቦታዎች በልዩ ሁኔታ መዘጋጀቱን ነው ዶክተር ከተማ የገለጹት።

ለፈተናው ደህነት ሲባልም ተማሪዎች የተከለከሉ ነገሮችን ይዘው እንዳይገቡ በጸጥታ አካላት እስፈላጊው ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

ተማሪዎቹ በበኩላቸው በተሰጠው መመሪያ መሰረት ለፈተና የሚስፈልጓቸውን ቁሶች ብቻ ይዘው ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።