ዓላማዬ መማርና ለአገር በእውቀቴ ውለታ መዋል ነው- 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱት የ85 ዓመት አዛውንት

146

መስከረም 27/ 2015 (ኢዜአ) የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ለመውሰድ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች ከትናንት ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲዎች እየገቡ ይገኛሉ።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ30 ሺህ በላይ የ12ኛ ተፈታኞች በመቀበል ላይ ነው።

ተማሪዎቹ ከሀድያና ከወላይታ ዞኖች የተውጣጡ ናቸው።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ ፈተናውን ከሚወስዱት ተፈታኞች መካከል ከወላይታ ዞን ባይራ ኮይሻ ወረዳ የመጡት የ85 ዓመቱ አቶ ባፋ ባጋጃ ይገኙበታል።

የስምንት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ባፋ ኑሮ ባደረሳባቸው ጫና እና ልጆቻውን አስተምረው ቁም ነገር ለማድረስ ሲሉ በ1949 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ትምህርታቸውን እንዳቋረጡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የ85 ዓመቱ አዛውንት በ2009 ዓ.ም ከ66 ዓመት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በድጋሚ በመጀመር በባይራ ኮይሻ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

"እውቀት መቅሰም በእድሜ አይገደብም" የሚሉት አቶ ባፋ ያቋረጡትን ትምህርት ከአምስት ዓመት በፊት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የጀግንነት መገለጫ የሆነው የአደንና ፈረስ ግልቢያ ልምድ አለኝ የሚሉት አዛውንቱ ዓላማዬ ግን መማርና ለአገር በእውቀቴ ውለታ መዋል ነው ይላሉ።

በፈተና ወቅትም በግቢው የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማከናወን ዝግጁ ሆነን መጥተናል ያሉት አቶ ባፋ ክልከላ የተደረገባቸውን ጉዳዮች በሚገባ መረዳታቸውን አመልክተዋል።

ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ሲሆን ከ975 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም