በመዲናዋ ባለፉት ሁለት ወራት 14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል-ቢሮው

177

መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት 14 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ለኢዜአ እንዳሉት የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ተሳትፎ ትልቅ እምርታ እያሳየ መጥቷል።

በዚህም ቢሮው ከሐምሌ እስከ ጳጉሜን ባሉት ወራት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 14 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከዕቅዱ በላይ አሳክቷል ብለዋል።

አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በገቢ መጠንም ሆነ በግብር ከፋዩ ተሳትፎ ትልቅ ለውጥ የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብር አሰባስብ ሂደቱ እንዲሻሻል ቢሮው በአግባቡ በታማኝነትና በወቅቱ ግዴታቸውን ለሚወጡ ግብር ከፋዮች ዕውቅናና ማበረታቻዎችን እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዕውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ልዩ አገልግሎት መስጫ መስኮት በማዘጋጀት በቅድሚያ የሚስተናገዱበት አሰራር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ሁሉም ግብር ከፋይ አርዓያ የሆኑ ግብር ከፋዮችን ፈለግ በመከተል ግዴታውን በታማኝነትና በወቅቱ እንዲፈጽሙ ጥሩ መነሳሳትን ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው ሃላፊው የጠቀሱት።

የመዲናዋ ነዋሪዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡና በጊዜው በመክፈል አገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም