በሩብ ዓመቱ ከ23ሺህ በላይ ለሚሆኑት አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤት ታድሰዋል – የከተማ አስተዳደሩ

105

መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የ23ሺህ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ቤት ጥገናና እድሳት መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፕላን ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳዲ ወዳጆ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት አስተደደሩ ዜጋ ተኮር የ60 እና 90 ቀን ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰዋል።

በተለይ ባለፈው የክረምት ወራት በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ ስራዎችና አገልግሎቶች ውጤታማ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።

የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤት እድሳትና ግንባታ በማከናወን ከ23ሺህ በላይ የሚሆኑትን የቤት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

በዚህም አስተዳደሩ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና የአብዛኛዎቹ ቤቶች እድሳትና ግንባታ በተቋማት፣ ባለሃብቶችና ድርጅቶች የተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተከናወኑ ዜጋ ተኮር ስራዎች የተቀናጀና የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበት መሆኑን የገለፁት ዶክተር ዳዲ፤ በዚህም የከተማዋ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን የተወጡበት አፈፃፀም ነበረ ብለዋል።

አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታን ከማስፈን ጀምሮ በማዕድ ማጋራትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

“በቀጣይ የ90 ቀናት ዕቅድ የከተማዋን የሜጋ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የተጀመሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅና ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እናደርጋለን” ነው ያሉት።

ለህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት በሚሰጡ የመስተዳድሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ላይ የተጀመሩ የአገልግሎት ማሻሻያ ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ዳዲ ገልጸዋል።

በዚህም የተገልጋዩን ህብረተሰብ ዕርካታ ለማረጋገጥ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ዲጂታላይዝ የማድረግ፣ አገልግሎቱን ከሰው ንክኪና ከሙስና  ነፃ የማድረግ ስራ በቀጣይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።