በዞኑ በበጋ መስኖ በ15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የስንዴ ልማት ይካሄዳል-መምሪያው

232

ጎንደር መስከረም 26/2015 (ኢዜአ ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት በ15 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ለማልማት የሚያስችል ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ለማስጀመር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ እንደተናገሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በሃገሪቱ ከውጭ የሚገባን ስንዴ በራስ አቅም ለማምረት የተቀመጠን ግብ ለማሳካት ታሳቢ ተደርጎ ይከናወናል።

በዞኑ የመስኖ መሬቶችንና የውሃ አማራጮችን በመለየት ከ40ሺ በላይ አርሶ አደሮችን በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ለማሳተፍ የሚያስችል የንቅናቄ መርሃ ግብሩ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

የስንዴ ልማቱ ባለሀብቶችን፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲን፣ ጎንደር ግብርና ምርምር ማእከልንና አርሶ አደሩን በማሳተፍ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል ።

ከሚለማው መሬት 675 ሽህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል ።

በመስኖ ልማቱ ለምርት እድገት የሚያገለግሉ 30ሺ ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲሁም 22ሺ ሊትር ፀረ ተባይ ኬሚካል ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ በተመረጡ ወረዳዎች በሚዘጋጁ ሞዴል የሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች በትራክተርና በኮምባይነር የታገዘ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ሀላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ለሚሳተፉ አርሶ አደሮች ከ700 በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የዞኑ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ ዳዊት አቡ ናቸው፡፡

ከ90 በላይ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ተቋማት  በህብረተሰቡ ተሳትፎ የጠረጋና የእድሳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃይለማርያም በበኩላቸው አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ቢኖሩም በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ተናግረዋል ።

የውሃ ሀብቶቹን በአግባቡ ጥቅም ላይ  አውሎ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን በማጠናከር እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ድጋፍ የሚያደርጉ  የምርምርና ሌሎች  ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ መስኖ በ2ሺ 534 ሄክታር መሬት ስንዴ መልማቱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም