የሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ሙያዊ መርህን የጣሰና ሰላምን ለማምጣት እንቅፋት የሚፈጥር ነው - ፕሮፌሰር ጃን አቢንክ

መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ሙያዊ መርህን የጣሰና ሰላም ለማምጣት በሚካሄዱ አካታች ውይይቶች ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥር በኔዘርላንድ የለይደን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና መልካም አስተዳደር ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ጃን አቢንክ ገለጹ።

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደው 51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ቤቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ የኢትዮጵያ ተወካዮች ሪፖርቱን አስመልክቶ የሰጡት ምላሽ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሲቋቋም ጀምሮ ይሁንታ የነፈገችው በተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ቡድን፤ያወጣው ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ያነገበና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት የሚፃረር መሆኑን በመግለጽ በጽኑ መቃወሟ ይታወሳል።

በኔዘርላንድ የለይደን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና መልካም አስተዳደር ኤመሪተስ ፕሮፌሰሩ ጃን አቢንክ እንደሚሉት፤ በሪፖርቱ የቀረበው ሃሳብ አመኔታ የለውም።

ሪፖርቱ በትክክለኛና ገለልተኛ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በኮሚሽኑ አባላት የግል ውይይት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ እንደሆነ ይሰማኛል ብለዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ሪፖርቱ በመካዱም ከእውነት የራቀና እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው ሲሉም ገልጸውታል።

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ይፋ ያደረጋቸው ሃሳቦች አስደንጋጭ፣ ፋይዳቢስ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ሂደት ሙያዊ መርህን ያልተከተሉና የሰላም ሂደት ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ለማወቅ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ በጋራ የተካሄደው ምርመራ በአንፃራዊነት ሚዛናዊ እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግስትም የሚኒስትሮች ግብረ-ሃይል በማቋቋም በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ክልል የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በመመርመር ጥፋት የፈጸሙ ኃይሎችን ተጠያቂ ለማድረግ ምርመራ ማካሄዱን ገልጸዋል።

ሆኖም ሰሞኑን በሰብዓዊ መብት ምርመራ የባለሙያዎች ኮሚሽን ይፋ የሆነው ሪፖርት አካታች ያልሆነና ከዚህ ቀደም ለተደረጉ በጎ ጥረቶች ዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

መንግስት ጦርነቱን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት የያዘው አቋም እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም