ኮሚሽኑ ከክልል መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የተሳካ የትውውቅና የትብብር ሂደቶችን ፈጥሯል- ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር

127

መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በእስካሁኑ ሂደት ከክልል መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የተሳካ የትውውቅና የትብብር ሂደቶችን መፍጠሩን ኮሚሽነር አምባሳደር መሃሙድ ድሪር ተናገሩ።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ እስካሁን ድረስ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ በተለይም ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ሰባት ወራትን ማስቆጠሩን አስታውሰው በእስካሁኑ ሂደት በክልሎች ተንቀሳቅሶ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የምክክሩ ዋነኛ ዓላማ መሰረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ማድርግ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር መሃሙድ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሯል ብለዋል።

በእስካሁኑ የኮሚሽኑ ዋና ዋና ስራዎች ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የሲቪል ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ከሌሎች ጋር የትውውቅ ስራዎች መከናወኑን ገልጸዋል።

ከክልል መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማህበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ጋር የትውውቅና የትብብር ሂደቶች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል።

ለምክክር ሂደቱ አጋዥ በሆኑ ስትራቴጂክ እቅዶች ዙሪያ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር ተደርጓል ነው ያሉት።

አገራዊ ምክክሩ 4 ምዕራፎች ያሉት መሆኑን ያብራሩት አምባሳደሩ በሂደቱ አካታች፣ ግልጽና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ የሚያስችሉ ጥሩ ጅምሮች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የሂደትና የትግበራ ምዕራፎችን መሰረት በማድረግ እየተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ምዕራፉን አጠናቆ በህዳር 2015 ዓ.ም የምክክር ምዕራፉ ይጀምራል ብለዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተለይም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ሁሉም ዝግጁ እንዲሆን ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም