ኢዜአና ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ግሩፕ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

629

መስከረም 26/ 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሩሲያው ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ግሩፕ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ።

በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂንና የሁለቱ ዜና አገልግሎቶች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ስምምነቱ ሁለቱም የዜና አገልግሎቶች ተጠቃሽ የሆኑ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመለዋወጥ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚካሄዱ ትልልቅ ኩነቶችን የዘገባ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚመለከቱ መረጃዎችን እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ ዜናዎችን  በእንግሊዘኛና በአረብኛ ቋንቋዎች እንደሚለዋወጡም ተገልጿል።

የኢዜአ የህዝብ  ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንድይራድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ኢዜአ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን በመዘገብ የሚታወቅ የዜና ተቋም ነው።

ከስፑትኒክ  ኢንተርናሽናል ሚዲያ ግሩፕ ጋር የተደረሰው ስምምነትም፤ ኢዜአ ከዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት እንደ ሀገር የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለዋል ነው ያሉት።

የስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ግሩፕ የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር ቫስሊይ ፖሽኮቭ በበኩላቸው፤ ኢዜአ በአንጋፋነት ከሚጠቀሱ የዜና አገልግሎቶች መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

የዛሬው ስምምነት ተቋማቸው ለረጅም ጊዜ ከአንጋፋው ኢዜአ ጋር ለመስራት የነበረውን ፍላጎት ያሳካ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ የዜና አገልግሎቶች በተለይ በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ የመጣውን የሀሰተኛ ዜና ስርጭት በተአማኒ መረጃዎች ለማክሸፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ይህም ሁለቱ ተቋማት በሚዲያ ተከታታዮች ዘንድ ያላቸውን አመኔታና ተቋማዊ አቅም እንደሚያጠናክር በመጠቆም።