ዩጋንዳ በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የሴካፋ እግር ኳስ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች

346


መስከረም 26/ 2015 (ኢዜአ) ዩጋንዳ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የእግር ኳስ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈች የመጀመሪያ አገር ሆናለች።

በአበበ በቂላ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው የእግር ኳስ ውድድር ከተጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በምድብ ሁለት በተደረገ ጨዋታ የዩጋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ ሱዳን አቻውን 4 ለ 1 አሸንፏል።

ለዩጋንዳ አራፋት ንኮላ 2 እንዲሁም ፓትሪክ ሲምቡሲና አቡባካሊ ዋሉሲምቢ አንድ አንድ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አብርሃም ኦኬኒ ለደቡብ ሱዳን ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

ውጤቱን ተከትሎ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።

ብሔራዊ ቡድኑ በምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታው ብሩንዲን 4 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታውን ከታንዛንያ አቻው ጋር ዛሬ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታው በሶማሊያ 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው።