የሽብር ቡድኖችን ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች ለማምከን የመንግስትና ህዝብን የጋራ ጥረት ይጠይቃል

149

መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃትና ሌሎችም የጥፋት ሃይሎች የሚጠነሰሱ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለማምከን የመንግስትና ህዝብን የጋራ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ “የማጠቃለያ ምእራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” በሚል ያዘጋጀው ሰነድ አንደኛው የጥፋት ስልቱ የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲፈፀም ማድረግ ነው።

በዚህ የጥፋት ስትራቴጂው ከገጠር አስከ ከተማ የኑሮ ምስቅልቅል እንዲፈጠርና ዜጎች በመንግስት ላይ በምሬት እንዲነሱ የማድረግ እቅድ ሰንቋል።

የግብርና ምርቶች እንዳይሰበሰቡ በገበያ የምረት እጥረትና የኑሮ ውድነትን ማስከተል የአሸባሪው የጥፋት ስልት ሆኖ ተቀምጧል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ፤ የኢኮኖሚ አሻጥር በብዙ መልኩ የሚተነተን አገርና ህዝብን የማዳከም የጥፋት ስልት መሆኑን ይናገራሉ።

በዋነኝነት ግን የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ወይም የሌሎችን ተልእኮ ለማሳካት ሲባል የሚፈፀም መሆኑን ያብራራሉ።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ በአሸባሪው ህወሃት የተሸረበው የኢኮኖሚ አሻጥር ከውስጥና ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር አገር የማፍረስ እቅድ መሆኑን ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒሸርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ፤ በኢኮኖሚ ዙሪያ የሚፈፀሙ አሻጥሮች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም በአሸባሪው ህወሃት የታቀደው ግን የግብርናን ጨምሮ ሌሎች የፍጆታ  ምርቶችን እንዳይመረቱ፣ እንዲወድሙ ወይም እንዲሰወሩ በማድረግ እጥረት መፍጠር መሆኑን ያብራራሉ።

የአሸባሪው ህወሀት እቅድም የራሱንና ከሌሎች የተቀበለውን የጥፋት እቅድ የማሳካት የጥፋት ስትራቴጂ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በአገር ላይ የሚደቀኑ የኢኮኖሚና መሰል አሻጥሮችን ለመመከት የመንግስትና ህዝብን የጋራ ጥረት እንዲሁም የሚዲያውን ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም