ኢትዮጵያና ሶማሊያ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚው ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትስስር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለጸ

77

መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሶማሊያ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትስስር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ፕሮፌሰር ሶንኮር ጌይረ ተናግረዋል፡፡

አገራቱ በቀጠናው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሶማሊያ የፌዴራሊዝምና የደህንነት ትንተና ኢንስቲትዩት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሶንኮር ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ሶንኮር ጌይረ ለኢዜአ እንደተናገሩት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቻቸውን በመያዝ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በአገራቱ የጋራ ተጠቃሚነት እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መምከራቸውን በማስታወስ በዋናነት የሽብር ስጋቶችንና ጽንፈኝነትን ለመከላከልና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ  ሶማሊያና ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ ችግሮችን በጋራ መመከት በሚጠይቅበት ወቅት ጉብኝት ማድረጋቸው ታሪካዊና ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የጸጥታ ችግር እንደተጋረጠባት በመጠቆም፣ ሶማሊያም ከአልሸባብ የሽብር ቡድንና ከሌሎች ውስጣዊና ቀጣናዊ ችግሮች ጋር እየተዋጋች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም አገራቱ አሁን ላይ የቀጠናውን ሰላም እውን ለማድረግና ትብብርን ለማጠናከር የጋራ አቋም መያዝ እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሁለቱ አገራት ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ትብብር ለመፍጠር ለዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታቸው ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡

በቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ መንግስት እና በኢትዮጵያ መካከል ጥሩ ግንኙነት እንደነበር  አስታውሰዋል።

የአሁኑ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድም የነበረውን ግንኙነት የበለጠ በማስፋት ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ማጠናከር አለባቸው ነው ያሉት።

ፕሮፌሰር ሶንኮር በጽኑ እንደሚያምኑት በጸጥታና ደህንነት ዙሪያ ያለውን ትብብር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለማስፋፋት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።

የምሰራቅ አፍሪካ አገራት ሰላሟና ደህንነቷ የተጠበቀ የአፍሪካ ቀንድን እውን ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ትብብር ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ታሳቢ ያላደረገ ማንኛውም ፖሊሲ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም