በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የባህልና የኢኮኖሚ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትብብር ማጠናከር ይገባል- የኬንያ ልዑካን ቡድን

95

መስከረም 26/2015/ኢዜአ/ በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የባህልና የኢኮኖሚ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚገባ በኢሬቻ በዓል ላይ ተሳታፊ የነበሩ የኬንያ ልዑካን ቡድን አባላት ተናገሩ።

ከኬንያ የትምህርት ማህበረሰብ፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎችን የወከሉ የኬኒያ ልዑካን ቡድን አባላት በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ተሳትፈዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ በድምቀት በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ተሳትፈዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባልና በንግድ ስራ የተሰማሩት ሞሃመድ አህመድ፤ የቀድሞው የኬንያ መሪ ጆሞ ኬንያታ  ከኢትዮጵያው ንጉስ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ለመወያየት በመኪና ያደረጉትን ታሪካዊ ጉዞ እርሳቸውም በኢሬቻ በዓል ላይ በመታደም እንደደገሙት ይናገራሉ።

ከናይሮቢ ተነስተው በመኪና ሰባት ቀናትን የወሰደ ጉዞ አድርገዋል፤ በጉዟቸውም በየመንገዳቸው ያገኙት ማህበረሰብ እንደ ወንድምና እህት በመቀበል ፍቅርንና አብሮነትን እንደለገሳቸው ገልጸዋል።

ሌላኛው የልዑካን ቡድኑ አባል ሙዚቀኛና የሰላም አምባሳደር ሌሞርቲ ሌሞር፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን ጠቅሰው አስደናቂ ህዝብና ባህል መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸው በተለይም ሁለቱ ሀገራት የቆየና ጥብቅ ወዳጅነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ያረጋገጡትም የሁለቱን አገሮች ህዝቦች የባህል፣ አኗኗርና ሌሎችም የሚያመሳስሉ መስተጋብሮችን ነው።

በኢሬቻ በዓል ላይ የአከባበር ስርአቱ፣ የባህል አልባሳት ድምቀትና የውበት መገለጫነት እንዲሁም ትእይንቶቹ በእጅጉ ቀልብ የሚገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኢሬቻ ያሉ ክብረ በዓላት በሌሎች ሀገራትም መስፋፋትና በጋራ መከበር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህም የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና ቀጣናዊ ትብብርን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል ከኢትዮጵያም ባለፈ የመላ አፍሪካ እንዲሁም የዓለም ቅርስ በመሆኑ ለጋራ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ልናውለው ይገባልም ነው ያሉት።

የኢሬቻ በዓልን አስደናቂ ትእይንቶች በቀጣይ በቱርካና ሀይቅና ሌሎችም አካባቢዎች እንዲከበር በማድረግ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የባህልና የኢኮኖሚ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል የልኡካን ቡድኑ አባላት።

በኢትዮጵያ የተመለከቱትን መልካም ተሞክሮና አስደናቂ ሁነት ለሀገራቸው ህዝቦች ለማጋራት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም