በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ ከ አምስት መቶ በላይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ትምህርት መስጠት ጀመሩ

117

ጭሮ፣መስከረም 25/2015(ኢዜአ)- በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በሕዝብ ተሳትፎ የተገነቡ 5 መቶ 79 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ትምህርት መስጠት መጀመራቸው ተገለጸ።

ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት የዞኑ ሕዝብ ባዋጣው 5 መቶ ሚሊዮን ብር መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አወል አብደላ እንደገለፁት የህብረተሰብ ተሳትፎ ውጤት የሆኑት ትምህርት ቤቶች በአራት ወራት ውስጥ የተገነቡ ናቸው።

በዞኑ 5 መቶ 20 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን አስታውሰው 5 መቶ 79 ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶቹ ከ120 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛተማሪዎችን ተቀብለው ትምህርት መጀመራቸውንም ገልፀዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የትኛውም የኑሮ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች መሰረታዊ የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙና የታለመው የትምህርት ጥራት መሬት እንዲይዝ ከፍተኛ አበርክቶ እንደላቸውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ላይ ተሳትፎ ካደረጉ ወላጆች መካከል ወይዘሮ ሂንዲሳር እስማኤልንና ወይዘሮ ሒንዲ መሀመድ የዞኑ ሕዝብ በሚችለው አቅም አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ህፃናት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ካገኙ ወደ ፊት የተወዳዳሪነት አቅማቸው የጎለበተ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የሚመጡ ህጻናት ከሌሎች ጋር እኩል የሆነ ትምህርት እንዲያገኙና በትውልዱ መካከል ክፍተት እንዳይኖር የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ባደረገው ርብርብ በራሱ ገንዘብና ጉልበት ህጻናቱን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ሆነዋል ነው  ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም