ኢትዮጵያ በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ታደርጋለች

173

መስከረም 26 /2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የእግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ያደርጋል።

ስድስት አገራትን እያሳተፈ ያለው የእግር ኳስ ውድድር መስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም መጀመሩ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ፣ሶማሊያ፣ታንዛንያ፣ዩጋንዳ፣ደቡብ ሱዳንና ብሩንዲ በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አገራት ናቸው።

በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር የአራተኛ ቀን ውሎ በምድብ አንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛንያ አቻው ጋር ከቀኑ 10 ሰአት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።

በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታው በሶማሊያ 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ 7 ሰአት በምድብ ሁለት ዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ዩጋንዳ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ብሩንዲን 4 ለ 0 ማሸነፏ አይዘነጋም።ውድድሩ እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

በሴካፋ ዞን የእግር ኳስ ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ አገራት በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ዞኑን ወክለው ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም