በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝቡን አብሮነት በማጠናከር የህግ የበላይነት ማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ከማድረግ አንጻር አበረታች ውጤት ተመዝግቧል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

121

አዳማ፣ መስከረም 25 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝቡን አብሮነት በማጠናከር የህግ የበላይነት ማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ከማድረግ አንጻር አበረታች ውጤት መመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የከተማዋን ሕዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረገጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች በ90 ቀን እቅድ ውስጥ መፈፀማቸውንም ተናግረዋል።

የጥፋት ተልዕኮ ፈፃሚዎች እቅዳቸውና ምኞታቸውን እንዳይሳካ ለማድረግ የተሻለ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።

May be an image of 2 people, people sitting, people standing and indoor

በህግ ማስከበርና ሰላም ማረጋገጥ ረገድ የተሻለ ስራ መሰራቱን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ዜጋ ተኮር የ60 እና 90 ቀን እቅድ በማውጣት አነስተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ማዕድ በማጋራት፣ በከተማ ግብርና፣ በፅዳትና ውበት የተሻሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ያሳዩት ተነሳሽነት የሕዝቡ አብሮነት እየተጠናከረ በመምጣቱ የተመዘገበ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ከሰው ንኪኪ ነፃ ለማድረግ አበረታች የዲጂታላይዜሽን ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ፣ በውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ በንግድ ፍቃድና እድሳት፣ በገቢ ግብር፣ በደንብ ማስከበር፣ የመሬት አስተዳደር የተሻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ከሙስና ነፃ ለማድረግ የዘርፍ ተቋማቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ ዲጂታል የመቀየሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታን ማስፈንን ጨምሮ የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የስራ እድል ፈጠራና የገበያ ትስስር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሪፎርም፣ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎንና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በልዩ ትኩረት የሚሰራባቸው ናቸው ብለዋል ከንቲባዋ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም