የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርገናል- ዩኒቨርሲቲዎች

127

መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ዩኒቨርሲቲዎች አስታወቁ፡፡

የ2014 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን በተሳካ መልኩ ለማካሄድ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን መግለጹም ይታወሳል፡፡

ኢዜአ የዩኒቨርሲቲዎችን ዝግጅት በሚመለከት የአዲስ አበባ፣ የኮተቤ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎችን ያነጋገረ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲዎቹም ፈተናውን በተሳካ መልኩ ለመፈተን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አማካሪ ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ፈተናውን መስጠት የሚያስችል የማስፈጸሚያ ዕቅድ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት፡፡

በዩኒቨርሲቲው ፈተናውን ለመውሰድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች መመደባቸውን ጠቁመው፤ የመፈተኛ ፣የመኝታ እና የመመገቢያ ቦታን ጨምሮ ይህን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሥሩ ባሉት ዘጠኝ የመፈተኛ ጣቢያዎች ላይ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ተማሪዎችን በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኮተቤ ትምህርት  ዩኒቨርሲቲ የአገልግሎትና ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽመልስ ዘውዴ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ፈተናውን ለመውሰድ ከ5 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎች መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡

ፈተናውን በተሳካ መልኩ ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ተፈታኞች ወደ ዩኒቨርሲቲው የተፈቀደላቸውን ቁሳቁስ ብቻ ይዘው መምጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት መገርሳ ቃሲም ናቸው።

2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ከመስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ  እንደሚሰጥ በወጣው መርሃ-ግብር ተመላክቷል፡፡

በዚህም የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከመስከረም 26 እስከ 28 ፈተናው በሚሰጥባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ሲሆን ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 02 ፈተና ወስደው ከጥቅምት 03 ጀምሮ ወደመጡበት እንደሚመለሱ ተጠቅሷል።

ከጥቅምት 05 እስከ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ፈተናውን የሚያጠናቅቁ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም