ዩኒቨርሲቲው ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቢሮ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

120

ሚዛን አማን፣ መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቢሮ ቁሳቁሶችን አበረከተ።

አዲስ ለተመሰረተው ክልል ከዩኒቨርሲቲው የተበረከቱት ቁሳቁሶች የቢሮ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።

በድጋፍ ማስረከብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ሥራዎቹ ባሻገር በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍም ማህበረሰቡን ለመደገፍ እየሰራ ነው።

በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ሆኖ ለተመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የተደረገው የማቋቋሚያ ቁሳቁስም የዚሁ ድጋፍ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።



ቀደም ሲል የክልል ምስረታ ሂደት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነቱ የሚጠበቅበትን ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የክልሉ መመስረት ለማህበረሰቡ የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ዩኒቨርሲቲው እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለወደፊቱም ከክልሉ ጋር አብሮ በመስራትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ይቀጥላል ብለዋል።

የዛሬው ድጋፍም ደረጃቸውን የጠበቁ የቢሮ ጠረጴዛዎችና ወንበሮችን ያካተተ ሲሆን በቁሳቁስ የሚደረገው ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋጁዋ ሳፒ ድጋፉን ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ሙስጠፋ እጅ ተረክበዋል።

ሃላፊው በዚሁ ጊዜ የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ላበረከተው ድጋፍ ምሥጋናቸውን በማቅረብ በቀጣይም ክልሉና ዩኒቨርሲቲው በጋራ መስራት በሚያስችሏቸው ተግባራት ላይ ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት በእውቀት ላይ ተመስርቶ ወደ ኢኮኖሚ መቀየር እንዲቻል የዩኒቨርሲቲው ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም