ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አገራቸውን በበጎ ለማስጠራት እንዲሰሩ ተጠየቀ

62
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አገራቸውን በዓለም መድረክ በበጎ ለማስጠራት መደመርን በተግባር እንዲያሳዩ ተጠየቀ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ከቡራዩ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች በበጎ ተግባር እያገለገሉ የሚገኙ ወጣቶች መደመርን በተግባር ለመቀየር ወጣቱ ከጥፋት ተቆጥቦ በጎ ተግባር ላይ እንዲያተኩር ጠይቀዋል። የ17 ዓመት ታዳጊው ኪሩቤል ገብሬ ከቡራዩና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖቹ ለጋሾች የሚያመጡትን ውሃ፣ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማስተባበር እየተሳተፈ ነው። የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ይህ ታዳጊ አገሩን በዓለም መድረክ በበጎ ተግባር ለማስጠራት ህልም እንዳለው በመግለጽ መደመር ለሱ ለተቸገሩት የቻሉትን ማድረግ ነው። በእሱ እድሜ ለሚገኙና ሌሎች ወጣቶች በጥፋት ሳይሆን በበጎ ተግባር በመሳተፍ የቻሉትን እንዲያደርጉም መክሯል። ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ናትናኤል ደረጀ "የተጎዳው ወገን የእኛ ነው እነሱ ሲኖሩ እኛ እንኖራለን እነሱ ካሌሉ የኛ መኖር ዋጋ የለውም" በማለት ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን ገልጿል። ወጣቱ መደመርን በመፈክር ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ሃሳብ በማክበር፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በተሰማራበት የስራ መስክ ተግቶ በመስራት በተግባር ሊያሳይ ይገባል ሲልም መክሯል። በቀጣይም ኢትዮጵያን ከፍ ሊያደርጉና በዓለም መድረክ ስሟን በበጎ ሊያስጠሩ የሚችሉ ተግባራትን በግልም ሆነ በቡድን እንደሚቀጥል ነው የተናገረው። ወጣት ጸሃይ ተሾመ "ሰው ሲደመር በችግርም ሆነ በደስታ በተግባር አብሮ መሆን እንጂ በስሜት መነዳት አይደለም" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። ቀደም ሲል አዲስ አበባ ውስጥ ሰዎች ሲደበደቡ አይቶ የማለፍ ሁኔታ እንደነበር በትዝብት ማየቷን በማንሳት አሁን ግን እርስ በእርስ የመረዳዳት ጅማሮዎች መኖራቸውን ተናግራለች። በበጎ ፈቃድ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች የሚያሳዩት ትህትና፣ ርህራሄ፣ ማጽናናትና ተጎጅዎችን መርዳት እጅግ የሚያስደስት ነው ያሉት ደግሞ አስተባባሪው አቶ አለማየሁ ታደሰ ናቸው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት በቅንነትና በህብረት አገሩን ሊያለማ ይገባል በማለት መደመርን በተግባር ማሳየት አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል ። አስተባባሩሪው ጨምረውም "መደመር ማለት ልብን ነጭ አድርጎ መቅረብ ነው፤ ለህብረተሰብም ሆነ ለአገር" መደመርን በቅንነት ተቀብሎ መተግበር እንደሆነ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም