በክልሉ በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

161

ሐረር፤ መስከረም 25 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ተግዳሮት እየሆኑ ያሉትን የመስሪያ ቦታና ከፋይናንስ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የተመራ ቡድን ከሐረሪ ክልል የካቢኔ አባላት ጋር ከስራ እድል ፈጠራ ፣ከኢንዱስትሪ ሰላምና ከተቋም ግንባታ አኳያ ያሉ አዳዲስ እሳቤዎች ላይ መክረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ወጣቱ ሃይል  አምራች እንዲሆን ተገቢው ስልጠናና ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችን በተገቢው ማሰልጠን ሀገርን መለወጥ ብሎም የህዝብ ቁጥሩን ስጋት ሳይሆን እድል የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል ፡፡

ለዚህም እንደ ሐረሪ ክልል በስራ እድል ፈጠራ ተግዳሮት እየሆነ ያለውን ከመስሪያ ቦታ እና ከፋይናንስ ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለማቃለል  የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ በሀገራችን ከ1ሺ 800 በላይ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ቢኖሩንም ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይል እያመረትን አይደለም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰልጣኙ የሚፈለገውን በቂ ክህሎት ይዞ እየወጣ ባለመሆኑ ክህሎት የሚፈጥር ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ችግር ለማቃለል ሚኒስቴሩ ገበያ መር ስርዓት ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊየን ወጣቶች ወደ ቴክኒክ እና ማሰልጠኛ ተቋማት ይገባሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሰልጣኞች በቆይታቸው ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት እና ክህሎት በተገቢው መንገድ ሰልጥነው እንዲወጡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሯ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሮዊ ሃብቶችን በስራ እድል ፈጠራ ላይ በማዋል በስልጠና በማገዝ ለማሳደግና ተደራሽ ለማድረግ መስሪያ ቤታቸው እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶችን በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅድሚያ የስራ አመለካከትና ባህሪ በመለወጥ ከጠባቂነት አስተሳሰብ  ማላቀቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ሃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን ናቸው።  

የክልሉ ባህል ፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው፤ የሚኒስቴሩ ድጋፍ በክልሉ የሚመረቱ የእደ ጥበብ ስራዎችን ይበልጥ ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም