የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ሂደት የብልጽግና ፓርቲ የላቀ ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል

133

መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ሂደት የብልጽግና ፓርቲ የላቀ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲል በጀግንነት መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ሠራዊት ደም መለገስ ታላቅ ክብርና ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ክብር በጀግንነት እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ደጋፊና ደጀን መሆን የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።

"ለአገር ባለውለታና የሕዝብ አለኝታ ደማችንን መለገሳችን ትንሹ ስጦታ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ በሁሉም መልኩ ድጋፍና እገዛ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ ሁለንተናዊ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ሂደት የላቀ ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በአንድ በኩል ለአገር ደኅንነት በሌላ በኩል የማልማት ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት መከበር ሲባል የምናደርገው ድጋፍና እገዛ ሁላችንንም የሚያኮራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም