ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና ልማት ባንክ የእንስሳት አልሚ ማኅበራትን በጋራ ለማደራጀት ተስማሙ

186

መስከረም 25 ቀን 2015 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለያዩ ከተሞች 90 የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ አልሚ ማኅበራትን በጋራ ማደራጀት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሸባባው እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

የስምምነቱን አተገባበር አስምልክቶ ከክልል ኅብረት ሥራ ማህበራት የተውጣጡና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ምክክር አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የእንስሳት ባለሙያዎች መር የህብረት ስራ ማህበራት ልማት መርኃ ግብር ይፋ አድርጉዋል።

ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሸባባው፤ የእንስሳት ሃብት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት እንዲሆን የእንስሳት ሃብትና ተዋጽኦ ልማትን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በከተሞች በእንስሳት ሳይንስ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማደራጀት የእንስሳት እና የእንስሳት ተዋጾኦ እየተስታዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶክተር ዮኃንስ አያሌው፤ ባንኩ የፖሊሲ ባንክ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን ይደግፋል ብለዋል።

የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ሳለ አቅሙን የሚመጥን ለውጥ ያልታየበት ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ያላትን የእንስሳት ሃብት በሚፈለገው ልክ አልምታ ከመጠቀም አንፃር ክፍተተ መኖሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክም በእንስሳትና የተዋጽኦ ልማት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኅብረት ስራ ኮሚሽን የኅብረት ስራ ማስፋፊያ ዳይሬክተሩ ድሪባ በቀለ፤ የፕሮጀክቱ እውን መሆን በእንስሳት ሳይንስ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዘመናዊ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም