የምርምር ስራዎችና የጥናት ህትመቶች ለዓለም ተደራሽ በማድረግ ቅቡልነታቸውን ማሳደግ ይገባል--ትምህርት ሚኒስቴር

329

መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት፣ ምርምር ተቋማትና በሙያ ማህበራት ለሚዘጋጁ የምርምር ጆርናሎች ግምገማና የእውቅና ስርዓት በማዘጋጀት ጥራትና ቅቡልነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በብሄራዊ ምርምር ጆርናሎች ግምገማና እውቅና አሰጣጥ ስርዓት፣ ተስፋዎቻቸው ዙሪያ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በከፍተኛ ትምህርት፣ በምርምር ተቋማትና በሙያ ማህበራት የሚሰሩ ምርምሮችንና የጥናት ህትመቶችን ለዓለም ተደራሽ በማድረግ ቅቡልነታቸውን ማሳደግ አንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ በምርምር ስራ የሚሳተፉ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች ቢኖሩም በአለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ የሚደረገው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥ የምርምር ጆርናሎች ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው በአገሪቱ በሚቋቋም የምርምር ጆርናሎች ድረ-ገጽ እና መረጃ ቋት ውስጥ እንዲመዘገቡና ተደራሽ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የምርምር ስራዎች በዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች መረጃ ቋት ውስጥ በስፋት እንዲካተቱ የሚያበረታታ የአሰራር ስርዓት ማበጀት እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ተነስቷል፡፡

የጆርናሎችን ጥራትና እይታ በሚያሳድግ ውድድርንና ትብብርን በሚያረጋግጥ መልኩ የምርምር ስራዎች ሊሰሩና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን ቢኖር (ዶ/ር) በበኩላቸው የጆርናሎች ግምገማና እውቅና አሰጣጥ ስርዓት የጆርናሎችን ጥራት እና እይታን በመጨመር በዓለም አቀፍ ምርምር መረጃ ስርዓት (International Indexing Databases) ለመካተት በትጋት እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ ከሚታተሙ 200 በላይ ምርምር ጆርናሎች መካከል ተገቢውን መስፈርት ያሟሉ 39ኙ እውቅና ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከምርምር ማዕከላትና ከሙያ ማህበራት የተወከሉ ተመራማሪዎችና የምርምር ጆርናል ዋና አርታኢዎች ተሳታፊዎች መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም