በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት በአይነትና በገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል

287

መስከረም 25 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅርቦት በአይነትና በገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ። 

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት አመት ለመድሃኒት አቅርቦት ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተጠቁሟል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት፣ ተደራሽነት፣ ጥራትና አቅርቦት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ የመድሃኒት አቅርቦት ነው።

የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በራሱ በጀት ገዝቶ በሽያጭ የሚያቀርባቸውና የጤና ሚኒስቴር ከሌሎች አካላት በሚያገኘው ድጋፍ የሚገዙ የመድሃኒት አቅርቦቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በአጠቃላይ 2014 በጀት አመት 51 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መድሃኒቶችን መገዛታቸውን አስታውሰው፤ ከዚህ መካከል 42 ቢሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶች ለጤና ተቋማት መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የኤች አይቪ፣ የወባና የቲቪ መድሃኒቶችን ጨምሮ በክምችት የ15 ቢሊዮን ብር መድሃኒት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዚህ አመት በመደበኛ በጀት ብቻ የ17 ቢሊዮን ብር መድሃኒት ለመግዛት እቅድ መያዙን ገልጸው፤ በጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በትብበር የሚፈጸመው ግዥ በ2014 አመት ከተፈጸመው ግዥ ብልጫ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የአእምሮ፣ ስኳር፣ ደም ግፊትና ሌሎች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መድሃኒቶችን ሙሉ ለሙሉ የማቅረብ እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።

እቅዱን ለማሳካት በጤናው ዘርፍና ከጤናው ዘርፍ ውጭ ያሉ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በግዥ ስርአቱ ቀልጣፋ አሰራርን ለመዘርጋት ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ከአየር መንገድ፣ ጉሙሩክና ሌሎች አካላት ጋር በትስስር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በስርጭት በኩልም መድሃኒት አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ለተጠቃሚው በፍጥነት እንዲደርስ ዘመናዊ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ጨምረዋል።