ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ተማሪዎች በራሳቸው ሰርተው የማለፍን ባህል እንዲያዳብሩ ያስችላል - የትምርት ሚኒስቴር

179

ባህርዳር፣ መስከረም 25 ቅን 2015 (ኢዜአ) "የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱ ተማሪዎች በራሳቸው ሰርተው የማለፍን ባህል እንዲያዳብሩ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ገለጹ።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለማስፈተን ያደረገውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ትናንት ማምሻውን የተመለከቱት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲፈተኑ የተደረገው ለሁለት ቁልፍ ዓላማዎች ነው።

የመጀመሪያው ተማሪዎች ፈተናን በራሳቸው ሰርተው ማለፍ የሚችሉበትን ባህልን መመለስ ሲሆን፣ ፈተናን ከማጭበርበርና ከስርቆት ነጻ የማድረግ ዓላማ አለው።

ከእዚህ በተጨማሪ ፈተናን በመስረቅ ወይም የተሳሳቱ መልሶችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት ተማሪዎች በራሳቸው ተማምነው እንዳይሰሩ የሚደረግበትንና የሚደርስባቸውን የስነ ልቦና ጫና ለማስቀረት እንደሚያስችል ዶክተር ፋንታ አስረድተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ እንደሚያስፈትን ጠቅሰው፤ ለዚህም  የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በአካል ተገኝተው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ የተማሪዎችን የመፈተኛ፣የመኝታና የመመገቢያ ክፍሎችን መጎብኘታቸውን ገልጸው ጥሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ብሔራዊ ፈተናው ያለምንም እንከን በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በየደረጃው ያለው አመራር ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር ከ60ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስፈትናል።

"በአሁኑ ወቅት ለተማሪዎች የመኝታ፣ የመመገቢያ፣ የመፈተኛና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች ዝግጅት ተጠናቋል" ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ በበኩላቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተማሪዎች ለፈተና ከሚመጡበት ትምህርት ቤት ጀምሮ መደረጉንና በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የትራንስፖርት ችግር በተወሰነ ደረጃ ሊገጥም እንደሚችል ጠቁመው፣"ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ርብርብ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

በአማራ ክልል ከ290 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና እንደሚቀመጡ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም