አካል ጉዳተኝነት የተቸገሩትን ከመርዳት አያግድም-አካል ጉዳተኞች

138
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 አካልጉዳተኝነት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተቸገሩትን ከመርዳት እንደማያግዳቸው   አካል ጉዳተኞች ተናገሩ። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ከቡራዩና አካባቢ ተፈናቅለው በአዲስ አበባ መድሃኔአለም ትምህርት ቤት ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለግሰዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች በወቅቱ እንደገለጹት ግጭቶች የሚያስከትሉት የአካል ጉዳትና ተያይዞ የሚመጣውን ተጽእኖ እናውቀዋለን ብለዋል። በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ መስኮች ተሳትፏቸው እየጨመረ ቢመጣም ተረጂዎችና መስራት የማይችሉ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ አሁንም ይንጸባረቃል ብለዋል በአስተያየታቸው። የዮዲና ሴት አካል ጉዳተኛ ማህበር አባል ወይዘሮ ዘርፌ ክንዴ እንዳሉት "አካል ጉዳተኛ የጎደለው አንዱ አካል በመሆኑ በአእምሮው ሰርቶ መኖር ይችላል"። ከዚህ ባለፈ ያለውን እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በወገኖች ላይ ችግር ሲያጋጥም ከመርዳት የሚያግደው የለም፤ "ችግሩ አስተሳሰቡ ላይ ነው" ብለዋለ። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን የቦርድ አባል አቶ ሱልጣን ቱሲ አካል ጉዳት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ የሚመጣ እንጂ ያለመቻል ምልክት አይደለም ይላሉ። የሰው ልጅ ሰርቶ መለወጥ የሚችለው እንዲሁም ሌሎችን የሚረዳው አዕምሮውን ተጠቅሞ በመሆኑ ጉዳት የሚያስከትለው "አይችሉምና ተረጂዎች ናቸው የሚለው አመለካከት ነው ብለዋል። እንደ አቶ ሱልጣን ገለጻ አካል ጉዳተኝነት የአካል እንጂ የአእምሮ ባለመሆኑ ሰርተው ሌሎች ሲቸገሩም ከመርዳት የሚያግዳቸው ሁኔታ የለም። ጉዳታችን የእጅ፣ እግር፣ መስማትና ሌሎች ጉዳቶች ቢሆንም  የምንችለውን በመስራት የቻልነውን እናደርጋለን ነው ያሉት። የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ማህበር አባል ወይዘሪት አድና አለባቸው ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞች ሰርተው የሚለወጡና ለችግረኞችም የአቅማቸውን  የሚያደርጉ መሆናቸውን ሊያጤን ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥታለች። "አካል ጉዳተኞች በአገራችን ተረጂዎች ብቻ አይደለንም" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው። አካል ጉዳተኞች የሚጠይቁት ግብዓት ከተሟላ ጉዳቱን ስለሚያውቁት ለተጎጂዎች ቀድመው ከመድረስ የሚያግዳቸው የለም የሚል ሃሳብ አላቸው። በቀጣይም በግጭቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ለመርዳት በሚደረገው ጥረት የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። በህብረተሰቡ ዘንድ "አካል ጉዳተኛ ተረጂ ነው" የሚለው አስተሳሰብ ሊፋቅልን ይገባል ሲሉም አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን መረጃ ያሳያል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም