በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብን ከጉዳት ለመከላከል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድሩ

136

ሐረር ፤ መስከረም 23/2015(ኢዜአ) ፡- በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብን ከጉዳት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የጀጎል ግንብ በዙሪያው ተጠግተው በተገነቡ የተሽከርካሪ እጥበት ቤቶችና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለጉዳት መጋለጡ ተመልክቷል።

ቅርሱን ለመታደግ የተቋቋመው ግብረ ሃይል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በስፍራው በመገኘት በተመለከቱበት ወቅት፤ በተለይ በቅርሱ ዙሪያ የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች እንዲዘጉ ርዕሰ-መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀጎል ቅርስን ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች በአንዳንድ ግለሰቦች መስተዋሉን ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቅሰዋል፡፡ 

ቅርሱን በተቀናጀ መልኩ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ግብረ ሃይሉ ከተለያዩ ተቋማትና ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን አበረታች ስራዎችን ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።

ግብረ-ሃይሉ ቅርሱን ከጉዳት ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት የመስተዳድሩ ድጋፍ እንደማይለየው አስታውቀዋል፡፡

የጀጎል ግንብን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው፤ የቅርስ አጠባበቅ ስታንዳርድ ህግ ጋር የሚጋጩ ግንባታዎች በጀጎል ግንብም ሆነ በዙሪያው እንዳይካሄድ ውሳኔ መተላለፉን በመጠቆም ሁሉን አቀፍ የቅርስ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የጀጎል ግንብን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግም ዙሪያውን በአረንጓዴ ልማት ከመሸፈን ባለፈ ውስጣዊ ክፍሉን ፅዱና ማራኪ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም