በቦረና ዞን የውሃ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የድርቁን ጉዳት ለመቋቋም ይሰራል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

204

መስከረም 23/2015 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተጀመሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ በድርቅ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም በትኩረት እንደሚሰራ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ የተመራ ልዑክ ከቦረና የአገር ሽማግሌዎች እና ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በመድረኩ በአካባቢው የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡት በዞኑ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ የግብረ- ሰናይ ድርጅቶች አስተባባሪ ፍጹም ደገሙ ድርቁ በተለይ በአንስሳቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ችግሩን ለመከላከል የመኖ አቅርቦት ተደራሽነት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

በድርቁ ምክንያት የእንስሳት ሃብታቸው የተጎዱባቸው ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሚጠበቀው መደበኛ ዝናብ ባለመኖሩ ምክንያት የውሃ እጥረት መከሰቱንም ነው ያነሱት፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት መንግሥት በድርቅ ሳቢያ በዞኑ የተከሰተውን የውሃ እጥረት ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በዞኑ ለበርካታ ዓመታት የተጓተተውን የቦረና የውሃ ፕሮጀክት በፍጥነት በማጠናቀቅ የውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ በአካባቢው በሚገኙ ስምንት ትምህርት ቤቶች የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ በማዘጋጀት የዝናብ ውሃንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን  ለተራዘመ ጊዜ ለመጠቀም እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም