የዩኒቨርስቲ ምሁራን በዲፕሎማሲው መስክ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

111

ጂንካ መስከረም 23/2015 (ኢዜአ) የዩኒቨርስቲ ምሁራን በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ ለሀገሪቱ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢፌዴሪ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባባሪያ ማዕከል ጠየቀ።

3ኛው በደቡብ ክልል የሚገኙ  የከፍተኛ  ትምህርት  ተቋማት  የጋራ ፎረም  በጂንካ  ዩኒቨርስቲ  አዘጋጅነት  ተካሂዷል ።

በማእከሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍና ክትትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን ሁሴን በፎረሙ ላይ እንደተናገሩት፤ እንደ ሀገር በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገቡ ባሉ አኩሪ ድሎች የዩኒቨርስቲ ምሁራን ሚና የላቀ ነው።

በተለይ ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ አንዳንድ የምራባውያን  ሀገራት  በኢትዮጵያ  ላይ ለማሳደር የሞከሩትን ተፅዕኖ ምሁራን ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠትና የሀሰት ዘመቻቸውን በማክሸፍ በጎ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

በተደጋጋሚ በውጭ  ሃይሎች የተቀነባበረውን ሴራ ለማጋለጥ ያደረጉት ርብርብ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የአገሪቱን እውነት ይበልጥ በማጉላት ሚናቸውን እንዲገፉበት አሳስበዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በገንዘብና በዓይነት ካበረከቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ነው ያወሱት።

ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል  እና የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው እንደገለጹት ፤ የሀገሪቱ  የሰላምና  የዴሞክራሲ  ሥርዓት ግንባታ ስር እንዲሰድና እንዲጎለብት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በተለይ ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ መልካም ሰብእና ያለው፣ በሀሳብ ልእልናና በሀቅ የሚያምን ተውልድ እንዲፈጠር ብዙ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  በአካባቢያቸው  የሚገኙ  ዕምቅ  የተፈጥሮ  ሀብቶችን  ፣የቱሪስት መስህቦችን እና ባህላዊ እሴቶችን በጥናትና ምርምር በመደገፍና ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን ለማስቻል ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አመላክተዋል።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ፎረሙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማሩን ሂደት ሠላማዊና ውጤታማ ለማድረግ  በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከሩን ነው የገለጹት።

የዩኒቨርሲቲዎች አካባቢያዊ ፎረም በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ብሎም በዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርዓትን ለማስረጽ አጋዥ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በተጨማሪም ፎረሙ  እስካሁን  በተለያዩ  ጥናትና  ምርምር  ስራዎች  ላይ የካበተ  ልምድ ለመለዋወጥ ያስቻለ መድረክ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የፎረሙ ተሳታፊዎች ለአንድ ቀን የተዘጋጀውን መድረክ ትናንት ማምሻውን ሲያጠናቅቁ ለስላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ስኬታማነት፣ የጥናትና ምርምር  ሥራዎችን  በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በማከናወን የየአከባቢያቸውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም በሀገሪቱ ላይ ከውሰጥና ከውጭ የሚቃጡ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ መንግሥት እየሰራ ያለውን ውጤማ ስራ ለማስቀጠል እንደሚተጉም ገልጸዋል።

በፎረሙ ከጂንካ፣ ዲላ፣ ዋቻሞ፣  ወልቂጤ ፣  ወራቤ፣  ሶዶና አርባ  ምንጭ ዩኒቨርስቲዎች  የተውጣጡ ምሁራንና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም   ከፌዴራል  እና ከክልል  የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም