በአፋር ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት መስጠት ተጀመረ

137

መስከረም 23/2015 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በህወሃት የሽብር ቡድን ወረራ ውስጥ በነበሩ 11 ወረዳዎች የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት የመስጠት ዘመቻ ተጀምሯል።

የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ በዋናነት የሚያጠቃው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣ በቫይረሱ በተበከለ ምግብ እና ውሃ አማካኝነት ወደ ሰውነት እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአፋር የተጀመረውም የክትባት መስጠት መርሃ-ግብሩ ለ4 ቀናት የሚቆይ ሲሆን እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ከ100 ሺህ በላይ ሕጻናት እንደሚከተቡም ተገልጿል።

የአፋር ክልል ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ ክትባቱን በማሂ-ረሱ ዞን ያንጉዲ ወረዳ አስጀምረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፈዉ አመት በ28 ወረዳዎች ከ187ሺ በላይ ህጻናት የመጀመሪያዉንና ሁለተኛውን ዙር የፓሊዮ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በወቅቱ በህዋሃት የሽብር ቡድን ወረራ ተይዘዉ በነበሩ 6 ወረዳዎች እና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ሌሎች ወረዳዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 11 ወረዳዎች ላይ ክትባቱ ሳይሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

አሁን በአካባቢዎቹ የጸጥታ ሁኔታዉ አንጻራዊ መሻሻል በማሳየቱ የመጀመሪያዉ ዙር የፓሊዮ መከላከያ ክትባት ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 4 ቀናት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

ክትባቱ በየአካባቢዎቹ በሚገኙ ጤና ተቋማትና የተመረጡ ህዝብ የሚበዛባቸው ማዕከሎችን ጨምሮ ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ከተወሰኑ ወራት በኋላም ሁሉተኛዉ ዙር ክትባት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

ለክትባት ዘመቻ ስራዉ ስኬታማነት ከክልሉ ኮማንድ ፖስት ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድም ቅድመ-ዝግጅት መደረጉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ከልጅነት ልምሻ በሽታ ለመታደግ ክትባቱን እንዲያስከትቡ ጥሪ ያቀረቡት ዳይሬክተሩ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ለክትባቱ ውጤታማነት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፖሊዮ (ፖሊዮሚለትስ) ተብሎ የሚጠራው የልጅነት ልምሻ በሽታ እ.አ.አ በ1800 አካባቢ እንደተከሰተ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም