ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመላው አፍሪካ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በፓን-አፍሪካኒዝም ዙሪያ ይወያያሉ-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

170

መስከረም 23/2015 /ኢዜአ/ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመላው አፍሪካ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በፓን-አፍሪካኒዝም ዙሪያ እንደሚወያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎች "የአፍሪካ የወንድማማችነት ምሽት" እየተካሄደ ሲሆን፤ በዚህም በሱዳን፣ አልጄሪያ፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎች መርሃ-ግብሩ ተከናውኗል፡፡

ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በተካሄደው መርሃ-ግብር ላይም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ፍስሃ ሻወል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመላው አፍሪካ አገራት ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በፓን-አፍሪካኒዝም ዙሪያ የሚወያዩበት መድረክ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠንካራ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ያላቸው መሪ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በጉባኤውም የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤና ለአፍሪካ ያላቸውን ራዕይ በተመለከተም ገላጻ ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡

መድረኩም "የአፍሪካ የመጪው ዘመን መሪ ወጣቶች ጉባኤ" በሚል ስያሜ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ በጉባኤው የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች ተሞክሯቸውን እንደሚያካፍሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፓን-አፍሪካንዝም እሳቤ ነጻነቷና አንድነቷ የተጠበቀ እንዲሁም የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የበኩሏን ሚና ለመወጣት እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በወንድማማችነት ምሽት መርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉት በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ማትኮ ኡርሱላ በበኩላቸው፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የዘር መለያየትና የአፓርታይድ ሥርዓትን እንዲታገሉ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩን ነው የገለጹት፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በጥር 2020 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡  

በተለይ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው፤  ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካል እና በቆዳ  ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ አንድነት ያላትን የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ ወንድማማችነት ምሽት መርሃ-ግብር የወጣቶች ተወካይ ይልማ ተረፈ በበኩሉ "የአፍሪካ የመጪው ዘመን መሪ ወጣቶች ጉባኤ" ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ የወደፊት መሪ የሆኑ ወጣቶች ፓን-አፍሪካኒዝም ራዕይን እንዲያጎለብቱ ማስቻል ስለመሆኑ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ወጣቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሆነም ጠቅሷል።

የአፍሪካ ወንድማማችነት ምሽት መርሃ-ግብር በቀጣይም በተለያዩ ኤምባሲዎች እንደሚቀጥል በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም