የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር አቅሙንና የተመራቂ ተማሪዎቹን ስራ የመቀጠር ምጣኔ አሳድጓል- ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና

171

መስከረም 23/2015 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር አቅሙንና የተመራቂ ተማሪዎቹን ስራ የመቀጠር ምጣኔ ማሳደጉን የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዩኒቨርሲቲው የምሩቃኑን የመቀጠር ምጣኔ ከማሳደጉ በተጨማሪ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር አቅሙን ወደ 2 ሺህ 200 አሳድጓል።

ዩኒቨርሲቲው የተሻለ የጽንሰ ሀሳብ ትምህርት እየሰጠ ቢሆንም በተግባር ተኮር ትምህርት ግን ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዩኒቨርሲተው ይህን ክፍተት ለመሙላት ከመማር ማስተማር ጋር የተያያዙ የሴኔት ሕጎችን በማሻሻል ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።

በተሻሻለው አሰራርም ማንኛውም አስተማሪ የተግባር ትምህርት መስጠት እና በጥናትና ምርምር መሳተፍ ብሎም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ተደንግጓል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ገንዘብን ጨምሮ አስፈላጊ ግብዓቶች የማሟላትና በዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ባላቸው የምርምር መፅሔቶች ለሚያሳትሙ ምሁራን ማበረታቻዎችን መስጠቱን አንስተዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው በዓመት እሰከ 20 ሚሊየን ብር ለምርምር በጀት ፈሰስ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

በዓመት የሚያሳትመውን የጥናትና ምርምር ብዛት ከ5 ዓመት በፊት ከነበረበት ከ400 ወደ 2 ሺህ 800 ማሳደጉን ነው የገለጹት።

'ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎትም አብሮ የሚጓዝ ነው' ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ እንደ አገር የተተገበረው የጤና ኤክስቴንሽን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ መመረቂያ የምርምር ውጤት መሆኑንም በአብነት አንስተዋል ።

የማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎም ለመምህራኑ ዕድገት ደረጃ መስፈርት 30 በመቶውን እንደሚሸፍን ገልጸው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ተሳትፎውን ያሳድጋል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠና ከመደበኛው ስርዓተ ትምህርት መስጠቱን ተናግረዋል።

ይህ አሰራርም የተማሪዎችን የመቀጠር ምጣኔ ከሶስት ዓመት በፊት ከነበረው ደረጃ ከፍ እንዲል ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

የትምህርት ተቋማት ምሩቃን በቂ የተግባርና የክህሎት ስልጠናዎች አግኝተው ወደ ስራ ዓለም ካልገቡ አገራዊ ብክነት መሆኑን ጠቅሰው ይህ እንዳይሆን ውጤታማ ስራ ሰርተናል ብለዋል።

የምሩቃኑን የመቀጠር ምጣኔ ከማሳደግ ባሻገር በዓለም አቀፍ ተቋማት የመሳብ ዕድላቸውም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል ነው ያሉት።

የመቀጠር ምጣኔ ማደግ ሌላው ምክንያትም ተማሪዎች ዩኒቨርተሲውን ሲቀላቀሉ በሚፈልጉት ትምህርት ክፍል እንዲመደቡ መደረጉ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ዩኒቨርሰቲው ከተለያዩ የግል ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ተማሪዎች የተግባር ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማመቻቸቱ ሲመረቁ በቀላሉ ስራ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በ2014 የትምህርት ዘመን መጨረሻ ብቻ 37 ተማሪዎች ወደ ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ትምህርት ተቋማት እንደተላኩ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማንኛውም ተማሪ ከመመረቁ በፊት ለሶስት ወራት በግል ዘርፍ ላይ ለልምምድ መስራት እንዳለበት አሰራር ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ አሰራር መሰረትም የተወሰኑ የግል ዘርፍ ድርጅቶች ተማሪዎችን የመቀበል ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም